የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የዘጠኝ ወራት አፈጻጸሙን ለሚዲያዎች በገለጠበት የተቋሙ ሃላፊ የሆኑት ሳንዶካን ደበበ ከአጎዋ ጋር በተያያዘ የተዘጋ አንድም የኢንዱስትሪ ፓርክ አለመኖሩን ገልጸዋል።
የአጎዋ ነጻ የገበያ እድል ለኢትዮጵያ በመከልከሉ እና ሌሎች ተጨማሪ ምክንያቶች ሳቢያ የሼድ ቁጥራቸውን የቀነሱ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ስለመኖራቸው ጠቅሰዋል።
ሃገሬ ቴ.ቪ ስለጉዳዩ ያነጋገራቸው የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የማርኬቲንግ እና የኮሚዩኒኬሽን ሃላፊ የሆኑት ሄኖክ አስራት የአጎዋ ነጻ የገበያ እድል መከልከል አብዛኞቹ የኢንዱስትሪ ፓርኮቻችን መዳረሻ አሜሪካ በመሆኗ የኢንዱስትሪ ፓርኮቹ ላይ የራሱን ተጽእኖ ማሳደሩን ጠቁመውናል።
"ከአጎዋ ጋር ተያይዞ በዋነኝነት እንደችግር የሚነሳው ጉዳይ አብዛኞቹ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የሚገኙት ኩባንያዎች ብዙዎቹ ማለት ይቻላል የገበያ መዳረሻቸው አሜሪካ ነች።"
እነዚህ የገበያ መዳረሻቸውን አሜሪካ ያደረጉት የኢንዱስትሪ ፓርኮች የጨርቃ ጨርቅ ምርት ላይ ያተኮሩ እንደነበሩ ገልጸውልናል።
የአጎዋ የገበያ እድል መከልከሉ ሌሎች አማራጮችን ለማሰብ እና ለማግኘት እድል ሰጥቶናል ብለውናል። አሜሪካ ሃገራችንን ከአጎዋ ነጻ የገበያ እድል መሰረዟን ተከትሎ ቻይና የሰጠችን እድልን ለመጠቀም እየሰራን ነው ብለዋል።
አቶ ሄኖክ በተለይም ከቻይና ለግብርና ምርቶች የተሰጠውን የገበያ እድል ለመጠቀም ለግብርና ምርቶች ማምረቻነት ምቹ የሚሆኑ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ለማመቻቸት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ለግብርና ምርቶች ኢንዱስትሪነት ምቹ የሆኑትን ፓርኮች ወደ ግብርና ኢንዱስትሪነት ለመቀየር ጥናት እየተደረገ መሆኑንም ጠቁመውናል።
የግብርና ምርቶች ላይ የሚሰሩ የኢንዱስትሪ ፓርኮች በክልል መንግስታት እየተገነቡ መሆናቸውንም አክለዋል።
ምንም እንኳን አሜሪካ ከአጎዋ የገበያ እድል ተጠቃሚነት ብታግደንም ከስምንት እስከ ሰላሳ በመቶ ቀረጥ በመክፈል ድርጂቶች ምርታቸውን ለአሜሪካ ገበያ በተወዳዳሪነት እንዲያቀርቡ መንግስት ሲያመቻችላቸው ቆይቷል ብለውናል።
በአብርሃም በለጠ
2022-05-16
