ዛሬ በዓለም አቀፍ ደረጃ የብርሀን ቀን የሚከበርበት ዕለት ነው። ብርሀን በሕይወታችን ውስጥ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል. በቀላሉ ጨለማን ለማስወገድ ከተፈጥሮ ባለፈ ሰው ሰራሽ ብርሀንን በርካቶቻችን እንጠቀማለን። ያለ ብርሀን የሰው ልጅ መኖር ይቻላቸው ይሆን?
ዩኔስኮ ባወጣው ጽሑፍ ብርሃን ሕይወት ነው። ብርሃን ከሌለ በፕላኔታችን ላይ ሕይወት አይኖርም ነበር ሲል የብርሀንን ጥቅም እንዲህ ባለ ቃል ገልጾታል። ብርሃንን በአስትሮፊዚክስ ስናጠና፣ ወደ ጥቂቶቹ እና ጥልቅ የአጽናፈ ዓለማት ሚስጥሮች እንገባለን።
የዛሬውም የብርሀን ቀን ይህን የሚዘክር ነው። በዋናነት በዚህ ዕለት ኢንጂኒየር እና ሳይንቲስት ቴዎዶር ማዪማን ይታሰብበታል፣ ይመሰገንበታል። ለምን ቢሉ በፈረንጆቹ 1960 የሌዘር ብርሀን አሊያም በሕክምናው፣ በንግዱ፣ በመገናኛ እንዲሁም በሌላውም ዘርፍ ጨቃሚ የሆነውን ብርሀናማ ጨረርን መስራት የቻለ ነው።
አሁን ላይ ብርሀን የምንለው ነገር ጨለማን ከመግፈፍ ባለፈ እጅግ አስደናቂ እና ልፋት አቅላይ ቴክኖሎጂ ተፈጥሮበታል በተለይም ቴዎዶር ማዪማን የፈለሰፈው የሌዘር ጨረር።
የዘንድሮ የብርሀን ቀን ዓለም አቀፍ የመሠረታዊ ሳይንሶች ዓመት ለዘላቂ ልማት በሚል መሪ ቃል በዓለም አቀፍ ደረጃ ተከብሯል።
በመሪ ቃሉ መሰረት ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ኪነ ጥበብ እንዲሁም ባህል እንዴት የተሻለ እና ሰላማዊ ማኀበረሰብ መፍጠር ይችላሉ በሚል ሀሳብ ውይይት ተካሔዷል። በተጨማሪ የብርሀን ቴክኖሎጂ በተጠቀሱት ዘርፍ ላይ ያለውን ሚና ይዳሰሳል።
ዕለቱን ከተለያዩ ሀገራት የተውጣጡ ሳይንስ ማኀበረሰብ፣ ተመራማሪዎች፣ እንዴት የተሻለች ዓለም እንፍጠር በሚለው ጉዳይ ምክክር እና ውይይት ያደርጉበታል።
የዚህ በዓል በዋናነት መከበር በብርሃን ላይ የተመሰረቱ ቴክኖሎጂዎች በሕይወታችን ውስጥ ስለሚጫወቱት ወሳኝ ሚና ግንዛቤ መፍጠር ነው።
ዓለም አቀፍ የብርሃን ቀን በዓለም ዙሪያ በሳይንስ ተደራሽነት፣ ትምህርትእና ማኀበረሰብ-ተኮር እርምጃዎችን እንደሚያጠናክር ቀኑን አስመልክቶ የወጡ መረጃዎች ያሳያሉ።
ዩኔስኮ ባወጣው መገለጭ ደግሞ ዕለቱ በመሠረታዊ ሳይንሶች እና በ ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ኢንጂነሪግ፣ ማቲማቲክስ ትምህርት ዓለም አቀፍ ትብብርን የማስተዋወቅ ተልእኮውን እንዲወጣ ዕድል እንደሚሰጥ ነው የገለጸው ።
በተጨማሪ የአለም አቀፍ የብርሃን ቀን በተለያዩ የሥራ እና የትምህርት ዘርፎች መካከል አዳዲስ ድልድዮችን ለመገንባት፣ ለኢንተር ዲሲፕሊን ሳይንስ ወሳኝ ፍላጎት ምላሽ ለመስጠት እና በዜጎች፣ ሳይንቲስቶች፣ ውሳኔ ሰጪዎች፣ የኢንዱስትሪ መሪዎች እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች መካከል የተሻሻለ ውይይት ለማድረግ አስተዋጽዖ ያደርጋል።
ዕለቱ የብርሃን ሳይንስ እና ቴክኖሎጂዎች በመላው ዓለም ባሉ ዜጎች ሕይወት ውስጥ የሚጫወቱትን ከፍተኛ ሚና ቀጣይነት እንዲኖረው የሚያበረታት ዓመታዊ በዓል ነው።
ይህ ብቻ አይደለም የሳይንስና ቴክኖሎጂን ገፅታ በማሳደግ፣ የትምህርት አበረታች ትግበራዎችን በማጉላት በዓለም አቀፍ ደረጃ የሕይወት ጥራትን በማሻሻል እና በዘላቂ ልማት ግቦች ላይ ትኩረቱን ያደረገውን የተባበሩት መንግሥታት የ2030 የዘላቂ ልማት አጀንዳ ማሳካትን ይጨምራል።
በሙሉጌታ በላይ
2022-05-16
