የልብ ህመም ማለት የልብ አካል ላይ በደረሰ ጉዳት ወይም የአሰራር ለዉጥ ምክንያት ለተለያዩ የሰዉነት ክፍሎች የሚሰራጨዉ ደም በቂ ሳይሆን ሲቀር የሚከሰት የጤና መታወክ ነዉ፡፡ የልብ ህመም ተፈጥሮአዊ ወይንም ከጊዜ በኋላ የሚመጣ ሊሆን ይችላል፡፡
ከልብ ደም ቧንቧ መጥበብ ጋር ተያይዞ የሚመጣዉ የልብ ሕመም በአብዛኛዉ በዕድሜ በገፉና በወንዶች ላይ ይከሰታል፡፡
ሌላኛው የህመሙ መንሳኤ ደግሞ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃና በተጨናነቀ አካባቢ የሚኖሩ ህፃናት በተደጋጋሚ በቶንሲል ህመም ይጠቃሉ፡፡ ለዚህ ቶንሲል በሽታ የተመረቱ አንቲቦዲ የተባሉ በሽታ ተከላካዮች ከልብ ቫልቮች መጥበብና መስፋት ጋር ተያይዞ ለልብ ድካም ይዳርጋሉ፡፡ ይህም በሀገራችን ዋነኛው የልብ በሽታ አይነት ነው ሲሉ የልብ ህክምና ባለሙያው ዶ/ር ደጁማ ያደታ ነግረውናል። በተጨማሪ በቤተሰብ ታሪክ ተመሳሳይ በሽታ መኖር፣ ሲጋራ ማጨስ፣ ከፍተኛ ደም ግፊት፣ ዉፍረት፣ ስኳር በሽታ፣ ኮሊስትሮል መብዛትና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አለማድረግ ለዚህ በሽታ የመጋለጥ ዕድልን ይጨምራል፡፡
ሲጋራ ማጨስ ለደም ቧንቧዎች መጥበብ እንደሚያጋልጥ በጥናት እንደተረጋገጠም ተሰምቷል።
ለረዥም ጊዜ ሳይታከም የቆየ ከፍተኛ የደም ግፊት የልብ ደም ቧንቧዎችን በማጥበብና የልብ ጡንቻዎችን በማወፈር ለልብ ህመም ይዳርጋል፡፡
ጤናማ ያልሆነ የአመጋገብ ሥርዓት ከእንሰሳት ተዋጽኦ የሚገኙ ስብና ቅባቶችን አብዝቶ መመገብ ደም ዉስጥ የኮሌስትሮል መጠንን ከፍ በማድረግ ለደም ቧንቧዎች ጥበት ይዳርጋል።
የልብ ድካም ቀላል የሆኑ አባባሽ ነገሮችን ከማከም እስከ ከፍተኛ የልብ ቀዶ ጥገና ህክምና ሊያስፈልገዉ ይችላል ። ሌላኛው አሳሳቢው ጉዳይ ደግም በሀገሪቱ ያለው የጤና ተቋም ከታካሚው ቁጥር ጋር መቃረን ነው ሲሉ የህክምና ባለሙያው ያብራራሉ።
በቀላሉ መድከምና አቅም ማጣት፣ ያለምንም እንቅስቃሴ ወይም መጠነኛ የአካል እንቅስቃሴ በሚያደርጉበት ሰዓት ትንፋሽ ማጠር ፣ ሌሊት ላይ የሚበረታ ሳል፣ እግር ማበጥ ወይም ከእግር የሚጀምር የሰዉነት ማበጥ የልብ መምታትና የትርታ መጨመር፣ ራስን መሳት፣ የደረት ህመም እንዲሁም የምግብ ፍላጎት መቀነስ፣ የሆድ መነፋትና ሆድ ህመም ዋና ዋናዎቹ ምልክቶቹ ናቸዉ፡፡
ቡና ለልብ ህመም ይዳርጋል ተብሎ በበርካቶች ሲነሳ እንሰማለን። ቡና የልብ ህመምን ባያስከትልም የልብ ህመም ያለባቸው ሰዎች ቡና ሲጠጡ ልባቸው ቶሎ ቶሎ የሚመታ ከሆነ ”ባይጠጡ” ብለው መክረዋል።
በህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የስርዓተ ጤና ከፍተኛ ተመራማሪ ዶ/ር አትኩሬ ደፋር እንደነገሩን በሀገራችን ወደ 4.5 ገዳማው ህዝብ ለበሽታው ተጋላጭ ነው ።
የታካሚውና የህክምና ተቋማት ቁጥር እንዳልተመጠጠነ በህክምና ባለሙያው የሚነሳውን ሀሳብ ተቋሙም እንደሚጋራው ሰምተናል ።
በህመሙ የተጠቁ ሰዎች ከባድ የሆነ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ባይመከረም መጠነኛ የሆነ እንቅስቃሴ ማዘዉተር እጅግ ጠቃሚ እንደሆነ የህክምና ባለሙያዎች ይመክራሉ።
በዓለም አቀፍ ደረጃ የልብ ሕመምን ጨምሮ ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች 41 ሚሊዮን ዜጎች ህይወታቸውን ያጣሉ።
በመቅደስ እንዳለ
2022-05-17
