ሶማሊያ የቀድሞ መሪዋን ሀሰን ሼክ መሀሙድ ፕሪዝዳንት አርጋ መምረጧን ይፋ ባደረገች ማግስት ከወደ አሜሪካ አንድ ነገር ተሰማ ።
አሜሪካ ወታደሮቿን ዳግም በሶማሊያ ልታሰማራ ነው የሚል ።
ከ 2017 ጀምሮ በስልጣን ላይ የሚገኙት የወቅቱ ፕሬዝዳንት መሀመድ አቡዳላሂ ፋርማጆ በምርጫው ተሸንፈው ለሀገሪቱ የፓርላማ አባላት ብቻ ክፍት የሆነው የመጨረሻ ድምጽ አሰጣጥ ሀሰን ሼክ መሀመድን የሶማልያ ፕሬዝጋንት አርጎ መሾሙ ይታወቃል ።
ተመራጩ ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሀሙድ በትላንትናው ዕለት ስራቸውን ሲጀምሩ ከአለም አቀፍ አጋሮች ጋር በቅርበት እንደሚሰሩ ተናግረዋል።
በቀውስ በምትናጠው የአፍሪካ ቀንድ አገር ሶማሊያ በድጋሚ በመመረጥ ሐሰን ሼይክ ሞሐሙድ ታሪክ ሠርተዋል። ነገር ግን ሶማሊያ ከረዥም ትግል በኋላ የመረጠችው አዲሱ ፕሬዝዳንት ከወደ ምዕራባዊያን እይታ ውስጥ ገብቷል ።
የቀድሞው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለረጅም ጊዜ በሀገሪቱ የቆዩትን የአሜሪካ ወታደሮች እንዲሁም ከ19,000 በላይ የአፍሪካ ህብረት ሰላም አስከባሪ ሃይሎች እንዲወጡ ባዘዙበት ወቅት ብዙዎች ላይ ስጋት አሳድሮ ነበር።
ታዲያ የ ሀገረ አሜሪካ ገዢው ጆ ባይደን የአሜሪካ ወታደሮች እንደገና ወደ ጎረቤታችን ሶማሊያ እንዲሰማሩ ፈቃድ ሰጥቻለሁ ብለዋል።
ፕሪዝዳንቱ የቀድሞውን ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሶማሊያ የነበሩ ወታደሮቻቸውን ለቀው እንዲወጡ ያዘዙትን ትዕዛዝ የሚጣረስ ነው።
ባይደን የሀገሪቱን ወታደሮች ወደ ሶማሊያ እንዲገቡ ከማድረግም ባሻገር ለ ሶማሊያ ራስምታት የፈጠሩትን የ አልሸባብ ሀይል በሀገራቸው ጥቁር መዝገብ ማስፈር ከ ዕቅዳቸው ውስጥ ተካቷል ።
አሁን ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ምን ያህል ወታደሮች ወደ ሶማሊያ እንደሚያሰማሩ ባይታወቅም፣ ነገር ግን ወታደሮቹ የልዩ ተልዕኮ ኃይል አባላት እና እዚያው ሶማሊያ ውስጥ የሚሰፍሩ እንደሚሆኑ ተገልጿል።
የፕሬዝዳንቱ ውሳኔ አሜሪካ ሠራዊቷን ከአፍጋኒስታን ካስወጣች በኋላ ጥያቄ ውስጥ ገብቶ የነበረውን የፀረ ሽብርተኝነት ዘመቻን መልሶ እንዲያንሰራራ የሚያደርግ ነው ተብሏል።
አዲሱ ተመራጭ ሶማሊያ ለ30 ዓመታት በእርስ በእርስ ጦርነት ስትናጥ አገሪቱን ጥለው ካልሄዱ ጥቂት መሪዎች መካከልም አንዱ ናቸው።
ከፍተኛ ድርቅን ጨምሮ በበርካታ ችግሮች የተከበበች አገር ከፋርማጆ የሚረከቡት ሼክ ሞሀመድ ከወዲሁ ብዙ ሀላፊነቶች ተጥሎባቸዋል ።
የተባበሩት መንግሥታት እንደሚለው ከ3.5 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በሩሃብ አፋፍ ላይ ሆነው አፋጣኝ የምግብ እርዳታ የሚጠብቁ ሲሆን ይህ በ አፋጣኝ ካልተገታ ችግሩ እየተባባሰ ይመጣል ።
በሌላ በኩል የኑሮ ውድነትና የዩክሬን ጦርነት ያባባሰው የዋጋ ግሽበትም መንግስታቸውን የሚፈትን ጉዳይ ነው ።
ታዲያ በሀገሬው ህዝብ ተወዳጅ የሆኑት አዲሱ ፕሬዝዳት ፈተናዎቹን ይወጡት ይሆን ።
በዮሴፍ ከበደ
2022-05-17
