ሀገሬ ቲቪ

ከአውሮፓ የሞት ሰማዕት ተልዕኮ የተረፉት

የዛሬዋ ዕለቱን ከታሪክ ወደ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ይወስደናል፡፡በዛሬዋ ዕለት ከ79 ዓመታት በፊት ወደ ተከናወነ ክስተት መለስ እንላለን ፡፡ አሜሪካ ከነእንግሊዝ እና ፈረንሳይ ጎን ቆማለች፡፡ ከናዚ ጀርመን ጋር ነው ውጊያው ፡፡ በአውሮፓውያኑ የሞት ሰማይ 25 ተልዕኮዎች ፈጽመው መመለስ ቻሉ የቢ-17 ሜምፊስ ቤሌ የቦንብ ጣይ አውሮፕላን ቡድን አባላት፡፡

በሁለተኛው የአለም ጦርነት አሜሪካ ከነእንግሊዝ ጎን በግልጽ ከቆመች በኋላ ቦምብ ጣይ ቡድኖቿን በብሪቴይን አስቀምጣለች።

አሜሪካ ወደ ጦርነቱ ከገባች ገና ወራት ናቸው በፈረንጆቹ 1942 እና 1943 የነበረው የአየር ጦርነት ለአሜሪካ የደም ኪሳራ ነበረው፤ ብሪቴይን በሌሊት በአውሮፓ ሰማይ ላይ ጥቃት ታደርሳለች። አሜሪካ ደግሞ በቀን።

የአሜሪካ አየር ሃይል አባላት በመጀመሪያዎቹ የአየር ላይ ጦርነት እስከ 80 በመቶ የሚደርስ ጉዳት ደርሶባቸዋል። የሜምፊስ ቤሌ ካፒቴይን ሞርጋን እንደሚለው ጠዋት ከ10 ሰው ቁርስ በልቶ ራት ከሁለት ሰው ጋር እንደመብላት ነበር።

ናዚ ጀርመን ኢላማቸውን የሚጠብቁ ጸረ አውሮፕላኖች አሉት። በዚህ ሁሉ መሃል አልፈው የቦምብ ጣይ አባላት የሞት ሰማይን ጥሰው ተልእኳቸውን መፈጸም ይኖርባቸዋል።

ታዲያ ከእነዚህ ቡድኖች የቦምብ ጣይ ቡድኖች ሜምፊስ ቤሌ የተሰኘው ቡድን አባላት 25 ተልእኮዎችን በአውሮፓ አድርገው ወደ አሜሪካ በመመለስ የመጀመሪያዎቹ የቦይንግ B – 17 አባላት መሆን ችለዋል። ይህም የሆነው በዛሬዋ እለት ከ79 አመታት በፊት ነበር።

በማይታሰበው የሞት ሰማይ የአውሮፕላኗ ካፒቴይን ሮበርት ሞርጋን እና ባልደረቦቹ 25 ተልእኮዎችን ፈጽመው በመመለስ ጭምር የመጀመሪያዎቹ ተርፈው ወደ አሜሪካ በህይወት መመለስ የቻሉ ቦምብ ጣዮች ሆነዋል። ናዚ ጀርመንን ለማሸነፍ የአሜሪካ አየር ሃይል ከባድ ቦምብ ጣዮች ላደረጉት ተጋድሎ የሜምፊስ ቤሌ አባላት ምልክት መሆን ችለዋል።

የሜምፊስ ቤሌ ቡድን የመጨረሻ እና 25ተኛ ተልእኮ የነበረው የናዚ ጀርመንን የሎሬንት የባህር ሰርጓጅ መርከብ ጣቢያ ማውደም ነበር።

ተልእኳቸውን ፈጽመው ወደ አሜሪካ ሊመለሱ ሲሉ የውጊያ ሜዳሊያ ሲቀበሉ የፊልም ምስል ተቀርጿል። ይህም በአሜሪካ የቦምብ ጣዮች ታሪክ ረዥሙ የዶክመንታሪ ምስል የተቀረጸበት አንዱ የታሪክ አጋጣሚ ነው። ድራማዊ የሆነ ቀረጻ ተከናውኖበታል።

የቦምብ ጣዮቹ በፓራሹት ሲወርዱ የሚያሳይ ቀረጻ ብሎም አንዱ ቦምብ ጣይ ከሌላኛው ጋር በመጋጨቱ የተቀረጸው ምስል ጥቃት አድርሶ ሲመለስ የሚመስል እይታንም መያዝ ችሏል።ይሁንና ግን ይሄው የሜምፊስ ቤሌ የዶኩመንታሪ ቀረጻ ለቀጣዮቹ 11 ወራት ለእይታ አልበቃም ነበር።

የቡድኑ አባላት ደጋግመው የቦምብ ጥቃት ሲያደርሱ የሚያሳይ በቂ ምስል ለዘጋቢ ፊልሙ እየተሰበሰበ ነበር። በጊዜው 25 ተልእኮ አንድ የቦምብ ጣይ ቡድን አድርጎ የመመለሱ ነገር ጠባብ ነበር። የሜምፊስ ቡድን የቦይንግ B-17 አባላት ግን 25ቱን ሞት የረበበት የአውሮፓ ሰማይ ተልእኮ ፈጽመው፤ በህይወት ተርፈው ወደ አሜሪካ ለመመለስ ችለዋል። ሜምፊስ ቤሌ አውሮፕላንም በክብር ተቀምጣለች። ከናዚ ጦር ጋር በአውሮፓ ሰማይ ስለተፋለሙት ፍልሚያም አባላቶቿ በክብር ይነሳሉ።

በሜምፊስ ቤሌ B-17 ተልእኮ ቀረጻ ላይ የተመረኮዘ ሜምፊስ ቤሌ የተሰኘ ፊልም እ.ኤ.አ. በ1990 በዊልያም ዋይለር በሆሊውድ እንዲሰራ ምክንያት ሆኗል። በዚህ ፊልም ላይ ጆን ሊትጎው፣ ማቲው ሞዲን እና ኤሪክ ስቶልትዝ ተውነውበታል።

በአብርሃም በለጠ
2022-05-17