ንግድ ሚንስቴር አሁን ላይ 446 ኢንዱስትሪዎች በቂ የውጪ ምንዛሬ ባለመኖር፣ በግብዓት ዕጥረት፣ በመሰረተ ልማት አለሟሟላት እና በተለያዩ ተያያዥ ተግዳሮቶች ምክንያት መዘጋታቸውን አስታውቋል። ከነዚህ ኢንዱስትሪዎች ውስጥ ደግሞ 118ቱ እንደገና መከፈታቸው እና ሥራ መጀመራቸውንም ሚንስቴር መሥሪያ ቤቱ ተናግሯል።
እዚህ ላይ አንድ ጥያቄ ማንሳት ተገቢ ይሆናል በነዚህ ኢንዱስትሪዎች ላይ የእንጀራ ገመዳቸው የተዘረጋ ዜጎች ጉዳይ ምን ይሆን?? የሚል። እኛም ይህን ጥያቄ አንግበን ለሠራተኛው መብት ለቆመው እና የሠራተኛው ጉዳይ ይመለከተኛል ወደሚለው የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኀበራት ኮንፌዴሬሽን(ኢሰማኮ) አቅንተናል።
የማኀበሩ ፐሬዝዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ እንደነገሩን ከሆን ፋብሪካዎቹ በኪሳራ ከተዘጉ ሠራተኞች ማኀበራት ኮንፌዴሬሽን ማድረግ የሚችለው መደራደር ነው ብለዋል። በዚህም ሰራተኞች ሌላ ሥራ እስኪያገኙ አዋጁ ከሚያስቀምጠው ከፍ ያለ ክፍያ ፍብሪካዎቹ እንዲሰጡ ድርድር ማድረጋቸውን ለጣቢያችን ተናግረዋል።
በዋናነት ተቋሙ የማኀበሩ አባላት ለሆኑ ሠራተኞች ቅድሚያ ሰጥቶ ነገሮችን እንደሚከታተል የሠራተኞች ማኀበራት ኮንፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ ነግረውናል። ያልተደራጁ እና የማኀበሩ አባላት ያልሆኑ ከስራ ገበታቸው የተበተኑ ሠራተኞች ቢኖሩም ቋማቸው ለነሱ መከራከር እንደማይችል ነው የገለጹልን። ኢትዮጵያ ከአጎዋ መብት በመሰረዟ ምክንያት በሀዋሳ ኢንዱስተሪ ፓርክ ኢፒክ የተባለ የአልባሳት ፋብሪካ ሥራውን በማቋርጥ 6 መቶ ሰራተኞቹን አሰናብቷል።
አንዳንድ ድርጅቶች በውጪ ምንዛሬ ዕጠረት ምክንያት በሙሉ አቅማችን እያመረትን አይደለም እና የውጪ ምንዛሬ ጠይቁልን የሚል አቤቱታዎች ለማኀበሩ መቅረቡን የተናገሩ አቶ ካሳሁን ይኽ ማለት ነገ ሠራተኛ ልንቀንስ ነውና እንድታውቁ የሚል መለዕክት ያለው ነው ብለዋል። አያይዘውም ከኢንዱስትሪ ፓርኮች እንዲቀነሱ የተደረጉ ሠራተኞች በሙሉ የድርድሩ ተጠቃሚ መሆናቸውን አቶ ካሳሁን ገልጸዋል።
ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ውጪ ባሉ ኢንዱስትሪዎች በሚገኙ የሠራተኞች ማኀበራት እስካሁን ከሥጋት ውጪ የደረሰን የሠራተኞች መሰናበት ሪፖርት የለም ብሏል የሠራተኞች ማኀበራት ኮንፌዴሬሽን።
በተጨማሪ የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኀበራት ኮንፌዴሬሽን ረቀቅ ያሉ ቴክኖሎጂዎችን እንጠቀማለን፤ሠራተኛው የሚሰራውን ሥራ በቴክኖሎጂው እንተካለን ባሉ እና ሠራተኛን በሚቀንሱ ኢንዱስትሪዎች ጠንከር ድርድር በማድረግ ሠራተኛው የ3 ዓመት ደሞዞ እንዲሰጠው አድርገናል ብለዋል።
ፋብሪካዎች እየተዘጉ ከሥራ ለሚሰናበቱ ሠራተኞች ከአጠቃላይ ደሞዝ አለፍ ያለ ገንዘብ እንዲያገኙ የማደረጉ ድርድር ዘላቂ መፍተሔ ሊሆን እንደማችል እናምናለን ያሉት የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኀበራት ኮንፌዴሬሽን ፕሬዝደንት አቶ ካሳሁን ፎሎ መንግሥት በጉዳዩ ሊያግዘን ይገባል ብለዋል። በአጎዋም ሆነ በሌሎች ምክንያቶች የሚዘጉ ኢንዱስትሪዎች ወደ ሥራ የሚመለሱበት መንገድ መመቻቸት እንዳለበትም አቶ ካሳሁን ጠቁመዋል።
በሙሉጌታ በላይ
2022-05-18
