ሀገሬ ቲቪ

ለሳንባ ካንሰር ታካሚዎች መፍትሄ ይሰጣል የተባለው ማሽን

የሳንባ ካንሰር በዓለም ላይ ካሉት የካንሰር አይነቶች ቅድሚያ የሚጠቀስ ሲሆን ይህም ለሞት የሚዳርግ ገዳይ የካንሰር ዓይነት ነው፡፡

የዓለም ጤና ድርጅት በጣም የተለመዱ እና ገዳይ የካንሰር በሽታዎች ብሎ በዝርዝር የጠቀሳቸውም የሳንባ፣ ጉበት፣ አንጀት፣ ሆድ እና ጡት ካንሰሮች ናቸው፡፡

የሳንባ ካንሰር (Lung cancer) ከቁጥጥር ውጭ በሆነ የሳንባ ሕዋሳት መመረት ምክንያት የሚመጣ በሽታ ሲሆን በመጨረሻም ካንሰራማ የሆነ የሳንባ እጢ በመመስረት የሳንባው ተግባር ይቀንሳል፡፡

ብዙ ጊዜ እንደሚገለጸው ሲጃራ ማጨስ የሳንባ ካንሰር ዋነኛ መንስኤ ነው፡፡ ይሁን እንጂ በጣም ብዙ የችግሩ መንስኤዎች አሉ ለምሳሌ ለኬሚካሎች እና ለካንሰር አምጭ ውህዶች መጋለጥ፣ የአየር ብክለት፣ ቤተሰብ ውስጥ ካንሰር ተጋላጭ ሰው ከነበረ እንዲሁም የእድሜ መግፋት ዋነኞቹ ናቸው፡፡

በሀገራችንም እንብዛም ያልተወራለት ነገር ግን በርካቶችን ካጠቁ የካንሰር አይነቶች ውስጥ ይመደባል፡፡ ሕብረተሰቡም ጋር ይሁን የጤና ባለሙያዎች ጋር ባለው ክፍተት ታካሚዎች የመጨረሻው ደረጃ ላይ ሲደርሱ ነው ወደ ጤና ተቋማት የሚመጡት ይላሉ በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የክሊኒካል ሰርቪስ ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር ራሄል አርጋው

“ለታካሚዎች መፍትሄ ይሆናል የተባለው ኢበስ የተሰኘው ማሽን ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ የሚደረገውን የታካሚዎች የናሙና ወሰዳ የሚያስቀር ነው፡፡”

የማቴዎስ ወልዱ የኢትዮጵያ የካንሰር ሶሳይቲ መስራች የሆኑት አቶ ወንዱ በቀለ በበኩላቸው በመልቲ ናሽናል ነን ካንሰር ፕሮጀክት የጤና ሚኒስትር፣ የማቴዎስ ወልዱ የኢትዮጵያ የካንሰር ሶሳይቲ ከቢኤምኤስኤፍ እና ቶራሲክ ሶሳይቲ በጋራ በመሆን በጋራ እየተተገበረ ነው ብለዋል፡፡

“በ2020 በሳንባ ካንሰር ላይ የተጀመረ ሲሆን በ4 ክልሎች ለጤና ባለሞያዎች ስልጠና መስጠት መረጃዎች በማደራጀት እንዲሁም ጥናት የማድረግ ስራዎች እየተሰራ ነው፡፡” ሲሉ አክለዋል፡፡

በዛሬው እለት የተመረቀውን የሳንባ ካንሰር ህክምና መስጫ 6.5 ሚሊዮን ብር ፈሰስ በማድረግ በአዲስ መልክ በማሰራት አዲሱን የኢበስ ማሽን ለማስጀመር በዝግጅት ላይ መሆኑን ሀገሬ ቴቪ በቦታው ተገኝቶ ተመልክቷል፡፡

አቶ ወንዱ በቀለ እንደነገሩን ከሆነለሦስት ዓመት የሚቆየው ፕሮጀክት በማቴዎስ ወልዱ የኢትዮጵያ የካንሰር ሶሳይቲ እየተመራ 1.8 ሚሊዮን ዶላር ተመድቦበት የሚንቀሳቀስ ፕሮጀክት ሲሆን ማዕከሉን ለማጠናከር እድሜው ሊራዘም እንደሚችል ሰምተናል፡፡

በፍሬህይወት ታደሰ
2022-05-18