ግዜው በተለይ ለምስራቅ አፍሪካ ጥሩ አይመስልም።
በእርስ በእርስ ጦርንርት፣ በአንበጣ መንጋ እንዲሁም በአየር ንብረት ለውት እየተፈተነች ባለችው ምስራቅ አፍሪካ ይህንንኑ ሰበብ አድርጎ በተጋረጠባት ድርቅ ሳቢያ ለሞት የሚዳረጉ ሰዎች ቁጥር እያስፈራን ነው ባይ የረዳኤት ድርጅቶች ተበራክተዋል።
አሁን ደግሞ በዚሁ አፍሪካ ቀንድ ቀጠና የሰብዓዊ ድጋፎችን የሚያደርጉት ኦክስፋም እና ሴቭ ዘ ችልድረን አዲስ ሪፖርትን እንካችሁ ብለዋል። ሪፖርቱ በምስራቅ አፍሪካ ከደቂቃ ባነሱ 48 ሰኮንዶች ውስጥ አንድ ሰው በቀተናው ለሞት ይዳረጋል ይላል።
በቀጠናው በሚገኙት ኢትዮጵያ፣ ኬኒያ እና ሶማሊያ በግጭት፣ በአየር ንብረት ለውጥ እና በምግብ ውድነት የተነሳ ሰዎች ለአጣዳፊ ረሀብ ተጋልጠዋል። የተራድኦ ድርጅቶቹ በጋራ ባወጡት መግለጫ እንዳሉት ዓለም መከላከል የሚችላቸውን አደጋዎች በቸልታ ማለፊን ያነሳሉ። አስቀድመን በጠቀስናቸው ሀገራትም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ለከፋ ችጋር ተጋልጠው ይገኛሉ።
ሀገራቱም የደረሰባቸውን አደጋ ብቻቸውን እንዲጋፈጡ ተገደዋልም ነው ያለው ሪፖርቱ። መግለጫው የምስራቅና ደቡብ አፍሪካ የህጻናት አድን ድርጅት ቃል አቀባይ ቻኮ ኪጋላን ጠቅሶ እንዳለው 5.7 ሚሊዮን ህጻናት በከፍተኛ የምግብ እጥረት እየተሰቃዩ ነው።በሦስቱ ሀገራት በከፍተኛ ርሃብ የሚሰቃዩ ሰዎች ቁጥር ካለፈው ዓመት ጀምሮ በእጥፍ ጨምሯል።
አስቀድሞ ከ10 ሚሊዮን የማይበልጥ የነበረው የረሀብ ተተቂዎች ቁጥር አሁን ላይ 23 ሚሊዮንን ተሻግሯል።እነዚሁ ሀገራት ያለባቸው የብድር ጫናም በሦስት እጥፍ አድጓል፤ እንደ ምዕራባውያኑ የዘመን ቀመር 2012 20.7 ቢሊዮን ዶላር ከነበረበት አሁን 65.3 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል።ይህም በቀጠርናው ያለውን የረሀብ አደጋ መከላከልን የበለጠ ስጋት ውስጥ ከቶታል።
ረሀብ የፖለቲካ ውድቀት ነው ያሉት የኦክስፋሙ ኃላፊ ብሪኤላ ቡቸር ለዚህም ምዕራባውያን ሀገራትን ተጠያቂ አድርገዋል። ድርጅቶቹ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ለኬንያ፣ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ የሚውል 4.4 ቢሊዮን ዶላር የገንዘብ ድጋፍ ለማግኘት ያቀረበውን ጥሪ የበለፀጉ ናቸው የሚባሉት ሰባቱ የዓለማችን ሀገራት እና ምዕራባውያኑ ሀገራት እንዲቀበሉ እና በቀጠናው እየረገፈ ያለውን የሰው ልጅ ህይወት እንዲታደጉ ተማፅነዋል።
ምዕራባውያን ሀገራት በግድ የለሽነት ባባሱት የአየር ንብረት ለውስጥ ሳቢያ በቀጠናው ለደረሰው ጉዳት ሊከፍሉ እንደሚገባ ሪፖርቱ ጠቁሟል። ከ2021-2022 እነዚህ ሀገራት ያሉ ባቸውን እዳዎችን በመሰረዝ ሰዎችን ማዳን እና የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የሚረዱ ሀብቶችን ነፃ ማድረግ አለባቸው ብሏል። አለበለዚያ ግን አይናችን እያየ ለሚረግፉ ነብሶች ተጠያቂዎች ከመሆን የሚያድነን አይኖርም።
በሳምሶን ገድሉ
2022-05-18
