ሀገሬ ቲቪ

እለቱን ከታሪክ - ‘‘የሚጨሰው ተራራ’’

ዛሬ እለቱን ከታሪክ በአለም የትላንት መዝገብ ከሰፈሩ የተፈጥሮ ሁነቶች አንዱን መለስ ብለን እንቃኛለን። ነገሩ የሆነው በዛሬዋ እለት ከ42 አመታት በፊት ነው። አንድ ተራራ ገና የቀኑ ጠዋትነት ሳይረፍድ ጨሰ። ከፍተኛ ፍንዳታ ተሰማ። እሳተ ገሞራም ሆነ።

ጊዜው በኛው አቆጣጠር 1972 ነው። በዚህ አመት በዛሬዋ እለት ጠዋት በዩናይትድ ስቴትስ ከዋሺንግተን ደቡብ ምዕራብ የሚገኘው የሴንት ሄለንስ ተራራ ዙሪያ ፍጥረታት ጸጥታ አልሆነላቸውም።

የአካባቢው ነዋሪዎች ሎዋላ ክላው ‘የሚጨሰው ተራራ’ ይሉታል። ለ 4 ሺህ 500 አመታት በየጊዜው የእሳተ ገሞራ ፍንዳታ አስተናግዷል።

ከ42 አመታት በፊት በዛሬዋ እለት ትልቁን ፍንዳታ ከማስተናገዱ አስቀድሞ ይሄው መንቀጥቀጥ እና መጨስ ልማዱ የሆነ ተራራ በሰሜናዊ ክፍሉ መንቀጥቀጥ ማሳየት ጀመረ። ኋላም መጠነኛ ፍንዳታ ታየበት። ቀጥሎ እንፋሎት ማስወጣት፣ አመድ መትፋት ያዘ።

በየለቱ ምልክቶች ይስተዋሉበት ጀመር፤ አጥኚዎች ውስጡ እየተናጠ እንደሆነ ገለጹ። የሚጨሰው ተራራ ሴንት ሄለን ሆድ እንደባሰው የተረዱ ባለስልጣናት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ከአካባቢው አሸሹ። ጥቂቶች አንሄድም አሉ።

የእሳተ ገሞራ ጫፍ የሆነው እና የ9680 ጫማ ከፍታ ያለው ይሄው ተራራ በፈረንጆቹ 1980 በዛሬዋ እለት እንደበፊቱ መቆም አልተቻለውም። ገና በጠዋቱ ከፍተኛ ፍንዳታ አስተናገደ። በ5 ማግኒቲውድ የመሬት መንቀጥቀጥ ፈተነው። አልቻለም። 210 ስኩየር ማይል የሚሆን ምድረ በዳ ወደመ። 57 ሰዎችም ለመሞታቸው ምክንያት ሆነ።

በታሪክ ከተመዘገበው ትልቁ የድንጋይ እና የበረዶ መንሸራተት ክስተት ከእንፋሎት እና የእሳተ ገሞራ ጋዞች ፍንዳታ ጋር ታጀቦ ወደ ሰሜን አቅጣጫ ገሰገሰ። እስከ ስድስት ማይል ርቀት ያሉትን ዛፎች አወደመ። 10 ሚሊዮን የሚደርሱ ዛፎች በሚጨሰው ተራራ ቁጣ ወደቁ። በቁጣው መንገዶች፣ ድልድዮች፣ ፓርኮች፣ ደኖች ወደሙ።

የፍንዳታው የአመድ ብናኝ ከተራራው ሰሜን ምዕራብ ለሚገኙ ከተሞች ተረፈ። ለሁለት ሳምንታት ለአለም ብናኙ ደርሷታል።በዚህ ትልቅ ፍንዳታ በሺዎች የሚቆጠሩ እንስሣት እና በሚሊዮን የሚቆጠሩ አሶች ሞተዋል። ሎዋላ ክላው ‘የሚጨሰው ተራራ’ ሴንት ሄለን የ1700 ጫማ ያክል ርዝመቱን አጣ። በፍንዳታው የነበረውን ሾጣጣ ቅርጽ አጥቶ ወደ ፈረስ ጫማ ቅርጽ ጎድጓዳነት ተቀየረ። ከፍንዳታው ሁለት አመታት በኋላ ሴንት ሄለን የሚጨሰው ተራራ ጥብቅ የምርምር ስፍራ እንዲሆን ተደረጓል።

በተራራው ምንም እንኳን አዲስ ጉልላት ከከፍተኛው ጫፍ አጠገብ ያለማቋረጥ እያደገ ቢመጣም ብሎም ትናንሽ የመሬት መንቀጥቀጦች በተደጋጋሚ ቢከሰቱም ተመራማሪዎች ከ42 አመታት በፊት የተከሰተውን አውዳሚ ፍንዳታ በቅርቡ ይደግማል ብለው አይጠብቁም።

በአብርሃም በለጠ
2022-05-18