በዓለማችን ላይ ስለእናት ፍቅር በርካታ ነገሮች ተብለዋል። አያሌ ሙዚቃዎች ተሞዝቀዋል፣ ለቁጥር የሚታክቱ ተውኔቶች ተተውነዋል ሌላም ሌላም። ይህም ሆኖ ግን የእናትን ፍቅር ጥልቀትን የሚገልጹ አይደሉም ሲባልላቸው እንሰማለን።እናት ለልጇ ምን ያህል መስዋዕትነትን ትከፍላለች? ጥያቄው በሁላችንም ልብ ውስጥ ይመለስ።እኛ ከወደ ማዘር ኢንዲያዎቹ ሀገር ህንድ አንዲት እናት ለልጇ ስትል 36 ዓመታትን እንደ ወንድ በመምሰል አሳልፋለች መባሉን ሰምተናል።
ይህች እናት ኤስ ፔትቻማል ትባላለች። በ 20 ዓመቷ ቤተሰቦቿ ለአንድ መልከመልካም ይድሯታል። የዚህች ምስኪን ትዳር ግን ከ15 ቀናት የተሻገረ አልነበረም። መልከመልካሙ ባለቤቷ በልብ ህመም ሳቢያ ከዚህ ዓለም ተለይቷት ይሄዳል።ታዲያ ከባለቤቷ ጋር በተዋበ የትዳር ሕይወት በቆየችባቸው ሁለት ሳምንታት በሆዷ ሴት ልጅ ፀንሳ ነበር። ዘጠኝ ወር በማህፀኗ የተሸከመቻትን ልጇን ከወለደች በኋላ የእሷን እና የሴት ሕፃን ልጇን ጉሮሮ ለመድፈን መስራት ነበረባት።
ነገር ግን የምትኖርበት በታሚል ናዱ ግዛት የምትገኘው ካቱናያክካንፓቲ መንደር ለዚህ እንድል አልሰጣትም።
ልጅን ካለ ወንድ እገዛ ለብቻ ማሳደግ ከነውርም በላይ ተደርጎ በሚቆጠርበት ማህበረሰብ ኤስ ፔትቻማል በርካታ ዘለፋዎችን እና ስድቦችን አስተናግዳለች። አንድ ቀን ተነስቼ ወደ ቤተመቅደስ አቀናሁ ትላለች ኤስ ፔትቻማል ፤ ከዚያም ፀጉሬን እንደ ወንዶቹ ተቆረጥኩ፣ የሴቶቹን ባህላዊ ልብስ፣ ሳሪዬን አውልቄ ሸሚዝ እና ሽርጤን አሸረጥኩ እራሴንም ሙቱ ስል ጠራሁት ስትል ግዜውን ታስታውሳለች። ነገር ግን ለዚህች እናት ይህ ሁሉ በቂ አልነበረም ተውልዳ ባደገችበት፣ ወግ ማዕረግ ባየችበት መንደር ውስጥ ይህ ሁሉ የእሷን ማንነት መለወጥ አይችልም። ስለዚህ ለእሷ እና ለልጇ ስትል ተወልዳ ካደገችበት መንደር እርቃ ማንም ወደ ማያውቃት አካባቢ አቀናች።
የእኔን ሴትነት የሚያውቁት ሴት ልጄ እና ተወልጄ ባደሁበት መንደር ውስጥ የሚኖሩት ዘመዶቼ ብቻ ናቸው ስትልም ትናገራለች። እኔ ከቀለም ቀቢነት ጀምሮ ሻይ እያዞሩ እስከ መሸት፣ በሱቅ ውስጥ እስከ መስራት ሁሉንም የስራ ዓይነቶች ያለመሰልቸት ሰርቻለው፤ ያለዕረፍት የሰራባቸውን ገንዘቦችም ለሴት ልጄ የወደፊት ህይወት ቆጥቤ አስቀምጥላት ነበር ስትል ለኒው ኢንዲያን ኤክስፕረስ ተናግራለች።
ታዲያ ሦስት አስርት ዓመታትን የከፈለችላት የዚህች መልካም እናት ሴት ልጅ ሻንሙጋሳንዳሪ አድጋለች፤ በወግ በማዕረግ ተድራም የራሷን ሕይወት መምራት ጀምራለች።
ህይወቷን ለልጇ አሳልፋ የሰተችው እናት ታዲያ አሁን ለፅናቷ በርካታ አድናቆቶችን እያገኘች ትገኛለች።
የዚህች እናት ታሪክ የአልቤኒያ መሃላ ሴቶችን እንድናስታውስ አድርጋናለች፤ ሙሉ ህይወታቸውን ለቤተእባቸው ሲሉ እንደ ወንድ በመምሰል የሚኖሩትን፤ በሌላ ግዜ እንመለስበታለን።
በሳምሶን ገድሉ
2022-05-18
