ፌስቡክ በተሰደዱ አናሳዎች ላይ ጥቃት እንዲፈጸም ያበረታታል በሚል 150 ቢሊዮን ዶላር ክስ ቀረበበት፡፡ በዩናይትድ ኪንግደም እና አሜሪካ የሚገኙ የሮሂንጊያ ስደተኞች ፌስቡክ የጥላቻ ንግግር እንዲሰራጭ ፈቅዷል በማለት ግዙፉን የማህበራዊ ሚዲያ ከሰዋል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2017 የቡዲስት አብላጫ ባለባት ማያናማር በተደረገ ወታደራዊ ዘመቻ 10ሺሕ የሚገመቱ የሮሂንጊያ ሙስሊሞች ተገድለዋል፡፡ ከዚህ ቀደም ፌስቡክ በ2018 በሮሂንጊያዎች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት እና የጥላቻ ንግግር ለመከላከል በቂ ስራ እንዳልሰራ መነገሩ ይታወሳል፡፡ በክሱ ላይ ኩባንያዉ ጥላቻ እና አደገኛ የሆኑ የተሳሳቱ መረጃዎች እንዲሰራጩ ለዓመታት እንዲቀጥል ፈቅዷል የሚል ቀርቧል፡ኩባንያው በሮሂንጊያ ላይ ጥቃት የሚቀሰቅሱትን ልጥፎችን ማውረድ ወይም መሰረዝ አልቻለም በበጎ አድራጎት ድርጅቶች እና በመገናኛ ብዙሃን ማስጠንቀቂያ ቢሰጥም ተገቢ እና ወቅታዊ እርምጃ መውሰድ አልቻለም መባሉ ቁጣን ቀስቅሷል፡፡ ፌስቡክ በማያንማር ከ20 ሚሊዮን በላይ ተጠቃሚዎች ያሉት ሲሆን ለአብዛኛዉ ሕዝብ የማህበራዊ ድህረ-ገጹ ዋንኛ የዜና ምንጭ ማጋሪያ ነዉ፡፡ አሁን ላይ ሜታ እየተባለ የሚጠራው ፌስቡክ ለቀረበበት ክስ ምላሽ ከመስጠት ተቆጥቧል፡፡
በሀገሬ ቲቪ
2021-12-07
