ሀገሬ ቲቪ

400 ጤና ጣቢያዎች ለድንገተኛ የቀዶ ህክምና አገልግሎት

400 ጤና ጣቢያዎች የድንገተኛ ቀዶ ህክምና አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ እየተሰራ ነው ተባለ።

ይህን ያሉት የጤና ሚኒስተር ሚኒስትር የሆኑት ዶ/ር ሊያ ታደሰ በ26ተኛው አመታዊ የኢትዮጵያ ቀዶ ህክምና ማህበር ስብሰባ ላይ ነው።

የድንገተኛ ቀዶ ህክምና አገልግሎት እንዲሰጡ ከታሰቡት ጤና ጣቢያወች መካከል 40 ያክል የሚሆኑት አገልግሎቱን መስጠት እንዲጀምሩ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።

ቀሪዎቹም ግብአት ተሟልቶላቸው አገልግሎቱን እንዲጀምሩ እንደሚደረግም ተናግረዋል። ከተመሰረተ የሩብ ክፍለ ዘመን እድሜ ያስቆጠረው የኢትዮጵያ ቀዶ ህክምና ማህበር 26ተኛ አመታዊ ስብሰባውን በዛሬው እለት ማካሄድ ጀምሯል።

የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የጤና ሚኒስተር ሚኒስትር የሆኑት ዶ/ር ሊያ ታደሰ ባለፉት ሁለት አመታት በተከሰተው የኮቪድ ወረርሽኝ ከጤናው ዘርፍ የቀዶ ህክምናው ዘርፍ ተጎጅ እንደነበር ገልጸዋል።

እንደጤና ሚኒስተር ከባለሙያዎች ጋር በመነጋገር እና በመተባበር የቀዶ ህክምና አገልግሎት አሰጣጡን ወደ ነበረበት ለመመለስ መቻሉን ገልጸዋል። ለዚህም የጤና ባለሙያወች ቁርጠኝነት ወሳኝ እንደነበር ጠቁመዋል።

ዶ/ር ሊያ አክለው በህልውና ዘመቻው በተለይም በጦርነት ቀጠናው የነበሩ የህክምና ባለሙያወች የሚያኮራ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን ተናግረዋል።

በጦርነቱ ወቅት ተጎጅዎች በቶሎ ህክምና ማግኘት እንዲችሉም ከጦርነቱ ቀጠና ውጭ የነበሩ በተለያዩ የሃገራችን ክፍሎች የሚገኙ የህክምና ተቋማት አገልግሎት እንዲሰጡ ስለመደረጉም ገልጸዋል።

የቀዶ ህክምና ተደራሽነትን ለማስፋት እየተሰራ እንደሆነ የተናገሩት ዶ/ር ሊያ የህክምና ባለሙያዎችን በምንፈልገው ልክ ወደ ስራ እያስገባን አይደለም ሲሉም ገልጸዋል።

በህክምና ስልጠና ወስደው የሚወጡ ባለሙያዎችም የሚፈለገው የሙያ ብቃት አለመኖር አንዱ ችግር እንደሆነ ገልጸው ያባለሙያዎች ብቁነት ላይ መስራት አስፈላጊ መሆኑን አመላክተዋል።

ከኢትዮጵያ ቀዶ ህክምና ማህበር ጋር በጋራ እንደሚሰሩ የገለጹት ዶ/ር ሊያ ለአጭር ጊዜ መፍትሄነት የህክምና ባለሙያዎች ከሶስት እስከ ስድስት ወር የሚደርስ ስልጠና ወስደው የድንገተኛ ቀዶ ህክምና አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ ለማድረግ ይሰራል ብለዋል።

በአብርሃም በለጠ
2022-05-19