ዛሬ ዕለቱን ከታሪክ አንድ ጥቁር አሜሪካዊ የተወለደበትን ቀን ይዘክራል። ታዋቂ የሰብዓዊ መብት ታጋይ፣ ቀንደኛ የሲቪል መብቶች እንቅስቃሴ አቀንቃኝ ነበር።
ይኽ ሰው ማልኮም ኤክስ ይባላል። ጥቁር አሜሪካዊው ማልኮም ኤክስ ለጥቁሮች መብት መከበር ብዙ ታግሏል። ብዙ ተከራክሯል። የአሜሪካ አንድ ግዛት በሆነችው ነብራስካ ‘’ኦምሀ’’ በምትባል ከተማ በፈረንጆቹ 1925 በዛሬዋ ዕለት ተወለደ።
አባቱ ሰባኪ እና የማርከስ ጋርቬይ ተከታይ እንደነበሩ ይነገርላቸዋል። በሚኖሩበት አካባቢ ‘’ኩ ክሉክስ ክላን’’ በሚባል የሚታወቀው እጅግ አክራሪ ጥቁር ጠል ቡድን በሚያደርስባቸው ማስፈራሪያ ቤተሰቡ ወደ ላንሲንግ ሚቺጋን መኖሪያውን ሊቀይር ግድ ሆነ።
በዚህም አካባቢ ቢሆን ጥቁር በመሆናቸው ብቻ የሚደርስባቸውን ያልተገባ ዛቻ እና ማስፈራሪያ አልቀረላቸውም ይብሱኑ 1931 የማልኮም ኤክስ ወላጅ አባት በነጭ አክራሪዎች ተገደለ።
የሀገሬው ሹማምንት በማልኮም ኤክስ አባት ግድያ ተሳለቁ። ግድያው የቀለም አሊያም የዘር ጥላቻ አይደልም አደጋ ነው ሲሉ አስተባበሉ።
እናታቸው ሉዊስ ሊትል እና ልጆቿ ምንም ዓይነት ካሳ ሳያገኙ ኑሮአቸውን ቀጠሉ። ከአባታቸው ሞት በኋላ ድህነት ሰተት ብሎ እነማልኮም ቤት ገባ ኑሮ እጅጉን ከባድ ቢሆንባቸው እናታቸው ሊትል መንገድ ላይ ምግብ በመሸጥ መተዳደር ጀመሩ።
ቢሆነም ግን ሉዊስ ሊትል ከፍተኛ የነርቭ ሕመም ስላጋጠማት ማልኮም ኤክስ በስድስት ዓመቱ ወደ ህጻናት ማሳደጊያ ማዕከል እንዲገባ ሆነ። አስተዋይ፣ ብልህ እና ጎበዝ ተማሪ እንደሆእ የሚነገርለት ማልኮም ስምንተኛ ክፍልን ተከታትሎ ትምህርቱን አቋርጧል።
ኋላም አደንዛዥ እጾችን ወደ መሸጥ ሥራ ውስጥ ተሠማራ። በዚህም ሳቢያ ወኅኒ መውረዱን ታሪክ ያስረዳል በዚህ ጊዜ ነበር በማልኮም ኤክስ ሕይወት ውስጥ አዲስ አስተምህሮ አዲስ ዐሳብ ብቅ ያለው። በወቅቱ የነበረ የእስልምና ትግል መሪ የኤልያስ መሐመድን አስተምህሮ እና ፍልስፍና ለመጀመሪያ ጊዜ የተዋወቀው። ጥቁር ሙስሊሞች ከጭቆና ጋር ስለሚያደርጉት ትግል ተረዳ። የትግል ታሪካቸው በልቡ ላይ ተጎዘጎዘ።
ከዚያም ማልኮም በስሙ መጨረሻ የ ኤክስ ምልክትን አደረገ የገዛ ስሙን የማይቀበለው የማይወደው መሆኑ ለማስገንዘብ ነው ሲል ነበር ይህን ማድረጉ።
ከስድስት ዓመት የእስር ቆይታ በኋላ በሀርለም ከተማ የአንድ መስጂድ መሪ ሊሆን ቻለ። አንደበተ ርዕቱ እና ሞገደኛ ንግግሩ ብዙ ተከታይ እና አድናቂን እንዲያገኝ አድርጎታል።
በፈረንጆቹ 1952 በአካባቢው 400 የነበረው የእስልምና ተከታይ ቁጥር በ1960 በ 100 ሺህ እጥፍ አድጎ 400 ሺህ ሊደርስ እንደቻለ ነው በጉዳዩ ላይ የተጻፉ ታሪኮች የሚያስረዱት።
በፈረንጆቹ 1964 ማልኮም ኤክስ ወደ መካ በመሔድ ሐጅ እንዳደረጉ ስለታሪክ የተጻፉ ድርሳናት ያስረዳሉ በዚህም ስሙን “ኤል-ሀጅ ማሊክ ኤል ሻባዝ” ብሎ ለወጦታል።
በማንኛውም መንገድ እና ሁናቴ ጥቁር አሜሪካውያን ባልንጀሮቹ እራሳቸውን ከነጮች ጭቆና እንዲከላከሉ ያሳስብ ነበር።
አንዳንዶች ታዲያ ይህ አካሔዱ ለጥቁር መብቶች መከበር ትልቅ ትግል በማድረግ ምሳሌ በመሆን ከሚታወቀው እና ህልም አለኝ በሚለው ንግግሩ የሚታወቀው ከማርቲን ሉተር ኪንግ አመጽ አልባ ትግል ጋር የተቃረነ ነው ሲሉ ይተቹታል።
ከቡድናቸው መሪ ኤልያስ መሐመድ ጋር በፖለቲካዊ ርዕዮተ ዓለም ላይ ከፍተኛ የሻከረ ግንኙነትን ተከትሎ በ1964 የፖለቲካ እና የሃይማኖት ቡድንን ለቋል። ማልኮም የእስልምና ትግል እና ጥያቄ የሲቪል መብቶችንም ጥያቄ ማካተት አለበት የሚለ አቋም ነበረው።
ከዚያም በኋላ የካቲት 21 ቀን 1965 በኒውዮርክ ከተማ በሚገኘው አውዱቦን ቦል ሩም ውስጥ የአፍሪካ-አሜሪካን አንድነት ድርጅት ሰልፍ ላይ በጥቁር ሙስሊም ተገደለ።
በሙሉጌታ በላይ
2022-05-19
