ሀገሬ ቲቪ

የአክሲዮን ገበያ መቋቋም

ኢትዮጵያ የራሷን የአክሲዮን ገበያ በማቋቋም ላይ ነች ተባለ።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ በአፍሪካ ቀንድ የመጀመሪያውን የአክሲዮን ልውውጥ ለማቋቋም ከኢትዮጵያ የገንዘብ ሚኒስቴር እና ከኤፍኤስዲ አፍሪካ ጋር ስምምነት መፈራረሙን አስታወቋል።

እንደ ምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ከሆነ የአክሲዮን ገበያ ማለት አክሲዮኖች የሚሸጡበትና የሚገዙበት ገበያ ማለት ነው፡፡ ይህ የአክሲዮን ገበያ ባለሀብቶች አክሲዮኖችን በእኩልነት መግዛትና መሸጥ እንዲችሉ ያስችላቸዋል ተብሎለታል። አዲሱ የአክሲዮን ልውውጥ በሀገሪቱ ውስጥ ኢንቨስትመንቶችን በማመቻቸት ረገድ ትልቅ ሚና ይጫወታል።

የኢትዮጵያ ኩባንያዎች እና ሥራ ፈጣሪዎች ለንግድ ሥራቸው የረጅም ጊዜ የብድር አማራጮችን እንዲያገኙ ያስችላል ሲል ቢዝነስ ኢንሳይደር ጽፏል። እንቅስቃሴው ወደ መሬት ሲወርድ ከ50 ያላነሱ የኢትዮጵያ ኩባንያዎች በገበያው ላይ ያላቸው ድርሻ ይዘረዝራሉ ተብሎ ይጠበቃል። ከእነዚህ ኩባንያዎች መካከል እንደ ኢትዮ ቴሌኮም እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ያሉ የመንግስት ኮርፖሬሽኖች እንደሚገኙበት መረጃው ከመናገር አልሸሸገም።

በመቅደስ እንዳለ
2022-05-20