ሀገሬ ቲቪ

እለቱን ከታሪክ

የዛሬው እለቱን ከታሪክ አንድ ሙዚቃን የሚዳስስ ነው። ሙዚቃው በዛሬዋ እለት በፈረንጆቹ 1983 የተለቀቀ ነው። ለዘጠኝ ሳምንታት በቢልቦርድ የምርጥ ሙዚቃዎች ሰንጠረዥ ውስጥ መካተት ችሏል። ይሄው ሙዚቃ ከ1980ዎቹ ምርጥ ሙዚቃዎች አንዱም ነው። Every Breath You Take ይሰኛል።

በፈረንጆቹ በ1983 ዘ ፖሊስ የተሰኘ የእንግሊዝ የሮክ ባንድ ሲንክሮኒሲቲ የተሰኘ አልበም አወጣ። በውስጡ ስቲንግ ተብሎ በሚጠራው ሙዚቀኛ እና የሙዚቃ ግጥም ጸሃፊ በሆነው ጎርደን ሰምነር የተጻፈ ‘Every Breath You Take’ የተሰኘ በጣም ተወዳጅ መሆን የቻለ ሙዚቃ አካቷል። ሙዚቃው ከዓመቱ ታላላቅ የሙዚቃ ስራዎች አንዱ መሆን ቻለ። ሙዚቃው በደንብ ከተሸጡ እና ተወዳጅ ከሆኑ የምንግዜም የ1980ዎቹ የሙዚቃ ስራዎች አንዱ ነው።

‘Every Breath You Take’ የተሰኘውን ሙዚቃ ስቲንግ ከቀድሞ ባለቤቱ ከፍራንሲስ ቶሜልቲ ተፋቶ ከትሩዲ ስታይለር ጋር አዲስ ግንኙነት በመሰረተበት ወቅት እንደጻፈው ይነገራል። ይሄው ተወዳጅ መሆን የቻለውን ሙዚቃ ሌሊት ተነስቶ በፒያኖ ላይ ሆኖ በግማሽ ሰዓት እንደጻፈው ይናገራል። የሚያጽናና የፍቅር ዘፈን የሚመስለው ሙዚቃው የሚተነፍሰውን ሁሉ የሚቆጣጠር ያለው ሃጢያተኛ ገጸባህሪ ድምጽ ይመስላል። ‘Every Breath You Take’ በወጣበት ዓመት ከምርጦቹ አንዱ ከመሆኑም በላይ የቢልቦርድ ምርጥ 100 ሙዚቃዎች ሰንጠረዥ ላይ ለስምንት ሳምንታት መካተት ቻለ።

በተሰራበት እንግሊዝ በምርጥ ነጠላዎች ሰንጠረዥ ለአራት ስምንታት ከቀዳሚዎቹ ተርታ መሆን ችሏል። በቢልቦርድ ምርጥ ትራኮች ዝርዝር ለዘጠኝ ሳምንታት መቆየት ችሏል። ይሄው ሙዚቃ በ26ተኛው የግራሚ የሙዚቃ ሽልማት ላይ በሶስት ዘርፎች ዕጩ መሆን ችሏል። የዓመቱ ሙዚቃ፣ የዓመቱ ሪከርድ ብሎም የዓምቱ ምርጥ በቡድን የተጫወተ ሙዚቃ በሚሉ ዘርፎች።

ሙዚቃውን የጻፈው ስቲንግ የዓመቱ ሙዚቃ ሽልማትን ሲወስድ፣ ሙዚቃውን የተጫወተው ባንድ ዘ ፖሊስ በቡድን የተጫወተ ሙዚቃ በሚለው ዘርፍ ሽልማቱን ወስዷል። ‘Every Breath You Take’ የምንጊዜም 500 ምርጥ ሙዚቃዎች የሮሊንግ ስቶን ዝርዝር 84ተኛው ሲሆን ከሮክ ሙዚቃዎች ተቀዳሚው ነው። ከቢልቦርድ ምርጥ 100 ሙዚቃዎችም 25ተኛው ሙዚቃ ራሱ ነው።

በፈረንጆቹ 1999 በቢኤምአይ የክፍለ ዘመኑ ምርጥ 100 ሙዚቃዎች መካከል 15ተኛው ቁጥር ላይ መቀመጥ ችሏል። ይሄንን ተወዳጅ መሆን የቻለ ሙዚቃ ስቲንግ በወጣ በሁለት ዓመቱ በቀጥታ ስርጭት በ1ነጥብ 9 ሚሊዮን ሰዎች ፊት ተጫውቶታል።

በአብርሃም በለጠ
2022-05-20