በተለይ የምዕራቡ ዓለም በስፋት ሲያደርገ ይስተዋላል። ለቤት እንስሳት ከሰው እኩል መብትን ማጎናፀፍ።
እነዚህን ባለመብት የቤት እንስሳት አይደለም መምታት እና ማባረር ቀርቶ ስርዓት ባለው መንገድ አልያዙም የተባሉ ሰዎች ፍርድ ቤት ሲገተሩ ማየት የተለመደ ነው።
ታዲያ አሁን የቤት ከምንላቸው እንስሳት ተሻግረናል፤ ለእነዚሁ ፍጥረታት መብት ቆመናል ያሉ ተሟጋቾች ለአንድ የዱር እንስሳ ዝርያ ይኄው መብት ካልተሰጠ ብለው ሙግት ላይ ናቸው።
የአሜሪካው ኒውዮርክ ከፍተኛ ፍርድ ቤትም በእነዚሁ ጉዳይ ተወጥሯል ነው የተባለው።
ፍርድ ቤቱ አንድ ዝሆን ከመካነ አራዊት እንዲወጣ እና እንዳሻው እንዲሆን መብት ሊሰጠው ይገባል በሚለው ክርክር እየተፈተነ ይገኛል።
በመካነ አራዊቶች ውስጥ ያለው ዝሆኑ ነፃ ሊወጣ ይገባል የሚሉት እነዚሁ የእንስሳት መብት ተሟጋቾች ምክንያታቸውንም ያስረዳሉ።
ከ51 ዓመታት በፊት ወደ ኒውዮርክ ከተማ መካነ አራዊት የመጣው የእስያ ዝሆን ነገር ቢያንገበግባቸው ወደ ፍርድ ቤት ማቅናታቸውን በመጥቀስ።
ሃፒ የሚሰኘው ይሄው ዝሆን ላለፉት 51 ዓመታት በከተማው በሚገኝ መካነ አራዊት ውስጥ እየኖረ ይገኛል።
ሃፒ ከሌሎች ዝሆኖች ተነጥሎ 4 ሺሕ ሜትር ስክዌር በሆነች ስፍራ ውስጥ ብቻውን እንዲኖር ተገዷል።
ከአራት ዓመት በፊት መቀመጫውን በፍሎሪዳ ግዛት ያደረገ አንድ የሰብዓዊ መብት ቡድን ባደረገው ጥናት ሃፒ በህገወጥ መንገድ ታድኖ ወደ አሜሪካ እንደመጣ አረጋግጧል።
ታዲያ አሁን የመብት ተሟጋቾቹ በህገወጥ መንገድ የታደነው ሃፒ ነፃነቱን ሊያገኝ እንደሚገባ እየተሟገቱለት ይገኛሉ።
ጉዳዩን ለመዳኘት የተሰየሙት ዳኞች ነገሩን በአፅኖት ለማየት እየሞከሩ ነው።
የዚሁ የሃፒ ጠበቃ መካነ አራዊቱ ይህንን ምስኪን ፍጥረት በሚገባ ሊጠብቀው አልቻለም፤ ይባሱኑም ሃፒን ለጉዳት እየዳረገው ይገኛል ሲሉ ተከራክረዋል።
ለአብነትም ከአንድም ሁለት ግዜ ሃፒ ጥቃቶች ደርሰውበት እንደነበር በማንሳት።
እንደ ምዕራባውያኑ የዘመን ቀመር በ2006 በሃፒ ላይ የተደረገ ጥናት እንዳመላከተው ከሆነ፤ እንስሳት ለራሳቸው ያላቸውን ግንዛቤ ለማወቅ የሚደረገውን በመስታወት ላይ እራስን መለየት በሚገባ ተወጥቷል።
ተሟጋች ቡድኑ ሃፒ ነገሮችን ከሰዎች ጋር መጋራትን የመሰለ በርካታ የማገናዘብ ችሎታ ባለቤትም ነው።
ከዚህ ቀደም ቺምፓንዚዎችን ጨምሮ ለእንስሳት ህጋዊ ሰውነት ለመስጠት የተደረገው ጥረት ባለመሳካት ተቋጭቷል።
ታዲያ አሁንም ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን በይደር አቆይቶታል። ሀፒን ነፃ ማውጣት በሚል የተጀመረው የእንስሳት መብት ተሟጋቾቹ እንቅስቃሴ ግን ሃፒን ነፃ ሳያደርግ አያባራም ተብሎለታል።
በሳምሶን ገድሉ
2022-05-20
