የሩሲያዊያንን ብሎም የሩሲያ አፍቃርያንን ያስደነገጠ አንድ መረጃ ከወደ ምዕራባዊያን ተሰማ ። ቆራጡ ሰው በጠና ታመዋል የሚል። ታዲያ በዚህ መረጃ ብዙዎች ተደናግጠዋል ። በዛው ልክ አይ ይሄማ የጠላት ወሬ ነው ባዩች ተበራክትዋል። ምክንያቱም ወሬው የተሰማው ከወደ ጠላት መንደር ነውና ። የዩክሬን ባለስልጣናት የሩስያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በደም ካንሰር እና በሌሎች ህመሞች በጠና ታመዋል ለዚህም እርግጠኞች ነን ሲሉ ድምጻቸውን አሰምተዋል።
የሁለቱ ሀገራት ጦርነት ከተጀመረ ወራቶች ተቆጥረዋል ። ታዲያ ቀውሱ ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ ፑቲን በጠና መታመማቸውን ምዕራባውያን እያራገቡት ይገኛሉ ። ብዙዎች የዚህን አይበገሬ መሪ መታመም አምነው ባይቀበሉትም የመረጃው ምንጮች በሚያወጡት ማስረጃ መደናገጥ ጀምረዋል ። ፑቲን ብዙውን ጊዜ በሚያዘወትርበት በ የበረዶ ሆኪ ሊግ ጨዋታ አልተገኙም ። ምንም እንኳን ፑቲን በበዓሉ ለሚሳተፉ እንግዶች በ ቪዲዮ መልዕክት ቢያስተላልፉም ይህ ነገር እውነት ይሆን እንዴ ባዮች እንዲበራከቱ አድርጓል ።
ከዚህም አልፎ ፑቲን ባለፈው ወር ከመከላከያ ሚኒስትሩ ሰርጌይ ሾይጉ ጋር ሲገናኙ ከፊታቸው ያለውን ጠረጴዛ በመያዝ በዝግታ ወደመቀመጫቸው ሲያመሩ የሚያሳይ አንድ ተንቀሳቃሽ ምስል ተሰራጭቶ ነበር ። በተሰራጨው ቪዲዮ ላይ ዘ ኪዩቭ ኢንዲፐንደንት የተሰኘው ድህረ ገጽ ዘጋቢ ኢሊያ ፖኖማሬንኮ እኔ ብቻ ነኝ ፑቲን ላይ የመታመም ነገር ያስተዋልኩት ወይስ የሌላም ሰው ስሜት ነው ሲል በ ትዊተር የማህበራው ትስስር ገጹ ላይ አስፍሯል ።
በቅርቡ የዩክሬን ወታደራዊ መረጃ ኃላፊ ሜጀር ጄነራል ኪሪሎ ቡዳኖቭ አሁን ላይ ፑቲን የከፋ ስነልቦናዊ ቀውስ ውስጥ ይገኛሉ ለዚህም ምክንያቱ ባጋጠማቸው የደም ካንሰር ህመም ነው ሲሉ ለስካይ ኒውስ ተናግረዋል ። የስካይ ኒውሱ ጋዜጠኛ ይህ ወሬ ምናልባት ፕሮፖጋንዳ ይሆን በማለት ላቀረበለት ጥያቄ ጀነራሉ "ይሄን ማጣራት ስራዬ ነው ያልተረጋገጠ መረጃ በፍጹም አላቀርብም" ሲሉ መልሰዋል ።
ነገሩ አውዛጋቢ ነው የ ዩክሬኑ ወታደራዊ መረጃ ኃላፊ እርግጠኛ ነኝ ፑቲን በቅርቡ ይቺን ዓለም ይሰናበታሉ ቢሉም ክሬምሊን ግን ይህ የጠላት ወሬ ነው ታላቁ ሰው ፑቲን ዛሬም በ መልካም ጤንነት ላይ ናቸው ወዳጆቻችን አትደናገጡ በማለት ድምጹን አሰምተዋል ።
የዩክሬኑ ወታደራዊ መረጃ ኃላፊ በቃለምልልሱ አክለውም "እመኑን ይህ ጦርነት በዓመቱ መጨረሻ ይጠናቀቃል ሩሲያ መሪዋን ከማጣት አልፋ ሽንፈትን ትክናነባለች በሰው ኃይል እና በጦር መሣሪያ ላይ ከፍተኛ ኪሳራ ደርሶባታል የመድፍ ጥቃቶች በተከሰቱበት ጊዜ ወታደሮቿ መሳሪያቸውን ትተው እግሬ አውጪኝ ብለዋል ሲሉ ተደምጠውዋል" ትላንት ለተለያዩ ሀገራት እርዱኝ የሚል ድምጽ ስታሰማ የነበረችው ዩክሬን ዛሬ ይሄን የልብ ልብ ከየት አገኘችው? እውነትም ቆራጡ ሰው ታመው ይሆን?
በዮሴፍ ከበደ
2022-05-20
