ሀገሬ ቲቪ

መንግሥት ቃሌን አላጥፍበትም ያለው ዝቅተኛ የደሞዝ ወለል ጉዳይ ከምን ደረሰ?

ባለፈው ወር ሚያዚያ 23/2014 በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከበረውን የሠራተኞች ቀን በሀገራችን ሲከበር አንድ ጉዳይ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት ሲነገር ነበር። ዝቅተኛ ደሞዝ ወለል። በእርግጥ ይኽ ጉዳይ ብዙ ጊዜ ሲነሳ ቆይቷል። መንግሥትም የምጋራው ጥያቄ ነው መፍትሔ እሰጥበታለሁ ካለ ቆይቷል። ነገር ግን እስካሁን ድረስ ሠራተኛን ከዚህ ደሞዝ በታች መቅጠር እንደማይቻል የሚያደርገውን የደሞዝ መጠን ማለትም “ዝቅተኛ ደሞዝ ወለል” አልተወሰነም።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በሚያዝያ ወር በተከበረው የሠራተኞች ቀን፤ ሠራተኛው በተለይም በኢንዱስትሪ ፓርክ ተቀጥረው የሚሠሩት በቂ የሆነ ደሞዝ እንደማይከፈላቸው ባደረኩት ጥናት አረጋግጫለሁ፤በዚህም ሠራተኞች በቂ የኑሮ ደረጃን የማግኘት መብታቸው አልተከበረም የሚል መግለጫን አውጥቶ ነበር። ስለዚህም የደሞዝ ወለል ለማስቀመጥ የተጀመረው ሒደት ይፋጠን ሲል አሳስቧል። በኮሚሽኑ የሲቪል እና ፖለቲካ መብቶች ኮሚሽነር የሆኑት ዶ/ር አብዲ ጅብሪል በኢትዮጵያ 49 በመቶ የሚሆነው ሠራተኛ ተቀጥሮ እየሠራ በድህነት ውስጥ የሚኖር ነው ብለውናል።

ኢትዮጵያ እስካሁን ዝቅተኛ የደሞዝ ወለልን አልወሰነችም ለምን ይኾን ይኽን የደሞዝ ወለል መወሰን ያልተቻለበት ምክንያት ስንል ጉዳዩን በይመለከተኛል የያዙትን ተቋማት ጠይቀናል። በሥራ እና ክህሎት ሚንስቴር የኢንዱስትሪ ግንኙነት ዳይሬክተር የሆኑት ሀና ማሩ የደሞዝ ወለሉ እንዲሁ በቀላሉ የሚወሰን አይደለም ቅድሚያ የሚሠሩ በርካት ሥራዎች በመኖራቸው ነው የሚል ምላሽ ሠጥተውናል። በተለይም የሀገሪቱ የምጣኔ ሀብት ሁኔታ የሚወሰነውን ዝቅተኛ የደሞዝ መጠን መሸከም የሚችል ነው ወይ የሚለው በጥንቃቄ መታየት ያለበት ነው ሲሉ ዳይሬክተሯ ገለጸዋል።

በሀገራችን ዝቅተኛ የደሞዝ ወለል ባለመኖሩ የአሠሪና ሠራተኛ አዋጁ ላይ እንደተቀመጠው አሠሪና ሠራተኛ በስምምነት ነው ሥራቸውን ሚከውኑት። የሀገሪቱን የምጣኔ ሀብት ሁኔታ ተመልክቶ እና ነባራዊ ሁኔታዎችን እያጠና የደሞዝ ወለል ይኽ መሆን አለበት ብሎ የሚወስን የደሞዝ ቦርድ እንደሚቋቋም ነው የተነገረው። አሁን ላይ ታዲያ ቦርዱን ለማማቋም የተዘጋጀውን ደንብ ለአስተያየት እንደቀረበ ነው የሰማነው

በጉዳዩ ላይ ያናገርነው የኢትዮጵያ ሠራተኞች ኮንፌዴሬሽን ላለፉት 15 ዓመታት ይኸው የደሞዝ ወለል እውን እንዲሆን ስጥር ቆይቻልሁ ብሎናል ለሚኒስትሮች ምክር ቤት የተላከውን የደሞዝ ቦርድን የሚወስነው ደንብ በ2013 ለጠቅላይ ሚንስቴር ጽ/ቤት የቀረበ ቢሆንም መንግሥት ከተመሠረተ በኋል ይታያል ቢባልም እስካሁን አለመታየቱን ነው የኮንፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ ለጣቢያችን የተናገሩት።

ፕሬዝዳንቱ አክለውም አሁን ላይ ባለው የኑሮ ውድነት ሠራተኛው እየፈተነ ነው ብለዋል። “አንድ ሺህ ብር ተክፍሎት ምንም ሊኖር አይችልም አይደለም በኑሮ ውድነት በደኀናውም ጊዜ በአንድ ሺህ ብር በኢትዮጵያ ውስጥ ሰው መኖር አይችልም’’ ያሉት አቶ ካሳሁን ደንቡ ይታያል ከተባልንበት ጊዜ በመዘግየቱ ግፊት እያደረግን ነው ብለዋል። ኮንፌዴሬሽኑ አሁን ላይ እንደነባራዊ ሁኔታ የሚከለስ እና ዝቅተኛ የደሞዝ ወለል ስንት መሆን አለበት የሚለወን የደሞዝ መጠን የውጪ አማካሪዎች ቀጥሮ ማስጠናቱን አቶ ካሳሁን ፎሎ ተነግረዋል።

ሰኔ 30፤ 2011 ዓ.ም በተሻሻለው የአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ ዝቅተኛ የደሞዝ አዋጅን አካቶ ጸድቋል።

በሙሉጌታ በላይ
2022-05-20