የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣የሳይንና የባህል ድርጅት(ዩኒስኮ) የህብረ ባህል መገለጫዎች ጥበቃና ልማት ስምምንት በ2005 መደንገጉ አይዘነጋም፡፡ ይሁን እንጂ ማሻሻያ በማስፈለጉ ብሎም የሀገራትን ሁኔታ ባገናዘበ መልኩ ከየሀገራት የሚቀርቡለትን ሪፖርቶች በማከል እንደየሀገራቱ ተጨማሪ ስምምነቶችን ያጸድቃል፡፡
የኢትዮጵያ የባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር ስር ሌሎች የመንግሥት ድርጅቶችን በማካተት፣22 የሚጠጉ የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች በጋራ የሰሩትን የ2021 3ተኛ ዓለም አቀፍ ሪፖርታቸውን ለሚመለከታቸው አካላት ይፋ አድርገዋል፡፡
የባህል እና ስፖርት ሚንስትር ዴኤታ የሆኑት ወ/ሮ ናፊሳ አልማሃዲ በባህልና ፈጠራ ኢንደስትሪ ዘርፍ አፈጻጸምና ተግዳሮቶች ላይ የወጣው ሪፖርትን ከፍተዋል፡፡
ሪፖርቶች ላይ ብዙ ጊዜ እንደሚባለው ፖሊሲዎች ይውጡ እንጂ ተፈጻሚነታቸው ላይ እምብዛም አይደሉም እንዲህ ያሉ በርካታ ማሻሻያ የሚደረግባቸው ሪፖርቶችም ከጠረጴዛ አያልፉም በሚል ወቀሳ ይቀርባል፡፡ በተለይ በባህል ዘርፍ ላይ የተለያዩ የተቀረጹ ፖሊሲዎች ቢኖሩም ተፈጻሚነታቸው ላይ ላለመሰራቱ ሚኒስትሩን ተጠያቂ ያደርጋል፡፡
በባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር የባህል ኢንደስትሪ ዳይሬክተር አቶ ተፈሪ ተክሉ የሚኒስትሩ ኃላፊነት ብቻ አይደለም ይላሉ፡
“የሚኒስትሩ ብቻ ችግር አይደለም በቅንጅት የሚሰሩ ናቸው፡፡ እኛ ጥረታችንን አላቆምንም።” በተጨማሪም ይህንን ሪፖርት ለመስራት የመረጃ እጥረት እና የማህበራት በአግባቡ አለመደራጀት ፈታኝ እንደሆነ ተነስቷል፡
እያንዳንዱ መረጃ የተሰበሰበው ከክልሎች መረጃ በመጠየቅ እና ዘመናዊ ባልሆነ መልኩ በመሆኑ የተሻለ አሰራር ያስፈልገዋል ተብሏል፡፡
እንደ አቶ ተፈሪ ከሆነ በዘርፉ የተደራጀ መረጃ እንዲኖር እና ሁሉም ፍትሃዊ መረጃዎችን እንዲያገኝ ብሎም እንዲህ ያለውን ችግር ይቀርፋል የተባለው የባህል ሳተላይት ለመስራት ሚኒስትሩ በዝግጅት ላይ መሆኑን ነግረውናል፡፡ “ሪሼፒንግ ፖሊሲ ፎር ክሬቲቪቲ” በሚል መሪ ቃል ሪፖርቱ በአለ ፈለገ ሰላም የስነጥበብ ትምህርት ቤት በተደረገው መርሃ ግብር ላይ ይፋ ተደርጓል፡፡
በፍሬህይወት ታደሰ
2022-05-20
