ሀገሬ ቲቪ

ተጠሪነቴ ለጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት ይሁን ያለው ተቋም

ቀድሞው የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ በአሁኑ የትምህርትና ስልጠና ባለስልጣን ተጠሪነቴ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት አሊያም ለጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ እየተባለ ለሚታወቀው እንጂ ለትምህርት ሚኒስቴር መሆን የለበትም አለ።

ተቋሙ ራሴን ችዬ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ባለመሆኔ ያጣሁት ብዙ ነው ሲል ለጣቢያችን ተናግሯል።ባለስልጣኑ በተለይም ከዓለም አቀፍ አቻ ተቋማት ጋር ግንኙነት እንዳይፈጥርና የልምድ ልውውጥ እንዳያደርግ የተጠሪነቱ ጉዳይ እክል ፈጥሮበታል።

አቶ ግርማይ አባዲ በተቋሙ የዕውቅና አሰጣጥ ከፍተኛ ባለሙያ እንደተናገሩት ከዓለም ተነጥሎ ያለ ባለስልጣን ነው፤ ለሚቆጣጠረው ተቋምም ተጥሪ መሆን የለበትም ብለዋል።

የትምህርትና ስልጠና ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አንዱዓለም አድማሴ እንዲሁ ተቆጣጣሪ ባለስልጣን ራሱን ችሎ መደራጀት አለበት ብለውናል። በመስሪያ ቤቱ የሚሰጡ አገልግሎቶች በዓለም ዐቀፍ ተቋማት ተዓማኒነት በማጣት ተገልጋዮችን ለእንግልት እየዳረጉ መሆኑን ዶ/ር አንዱዓለም አብራርተዋል።

ለመሆኑ ጥያቄያችሁን ለትምህርት ሚኒስቴር አቅርባችኋል ወይ ተብለው በሀገሬ ቴሌቭዥን የተጠየቁት ዳይሬክተሩ ጥያቄ አቅርበው ምላሽ እየተጠባበቁ መሆኑን አስረድተውናል።

ጉዳዩ የሚመለከተው የትምህርት ሚኒስቴርን ምላሽ ለማካተት በስልክም ሆነ በአካል ተደጋጋሚ ሙከራዎች ብናደርግም ምላሽ ሊሰጠን ፍቃደኛ አልሆነም።

በመቅደስ እንዳለ
2022-05-23