ሀገሬ ቲቪ

እለቱን ከታሪክ - ‘የጉለሌው ሰካራም ’ ደራሲ እና አርበኛ

የዛሬው እለቱን ከታሪክ በኢትዮጵያ የአጭር ልቦለድ ስነ ጽሁፍ ታሪክ ውስጥ ፈር ቀዳጅ የሆነ ደራሲን እንቃኛለን። ደራሲው ተመስገን ገብሬ ይባላል። በሁለተኛው የጣሊያን ወረራ ከጭፍጨፋ መሃል ተርፎ ለሃገሩ አርበኛ በመሆን አገልግሏል። ይሄው ደራሲ ለኢትዮጵያ ስነ ጽሁፍ የመጀመሪያ የሆነውን የጉለሌው ሰካራም አጭር ልቦለድን አበርክቶልናል። የተወለደው በዛሬዋ እለት በ1901 በደብረ ማርቆስ ነው።

121 አመታትን ወደ ኋላ መለስ ስንል በጎጃም ደብረ ማርቆስ አንድ ደራሲ እና አርበኛ ግንቦት 15/1901 ተወለደ። ይሄው ደራሲ ተመስገን ገብሬ ይባላል። በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የሆነው አጭር ልቦለድ የጉለሌው ሰካራም ደራሲ እና የሁለተኛው የጣሊያን ወረራ አርበኛ ነው።

ጣሊያን ኢትዮጵያን ድጋሜ ልትወር እንደምትችል የገባው ወጣቱ ተመስገን ገብሬ በየቦታው እየተዘዋወረ ንግግር ያደርግ ነበር። በጊዜው በሃገር ፍቅር ቴአትር ቤት ታዋቂ ንግግር አድራጊም ነው። ፋሽስት ጣሊያን ኢትዮጵያን ሊወር መሆኑን የተረዳው ተመስገን ልንወረር ስለሆነ ለጦርነት እንዘጋጅ የሚል ንግግርን ያደርግ ነበር።

ጣሊያን ኢትዮጵያን ወርራ ከያዘች በኋላ በየካቲት 12/1929 በተደረገው ጭፍጨፋ ዋነኛ በጣሊያን ሊያዝ የሚፈለግ ተጠርጣሪ ሆነ። አብርሃም ደቦጭ እና ሞገስ አስገዶም ግራዚያኒ ላይ ለሞከሩት የቦምብ ጥቃት ከጀርባ አለበት በሚል ዋነኛ ተፈላጊ ሆነ። በጣሊያኖች ይታደንም ጀመር።ብመጨረሻም በእጃቸው ገባ።

በጎጃም ደብረ ማርቆስ የተወለደው ተመስገን የቤተ ክህነት ትምህርትን ተከታትሏል። በቅኔ ትምህርትም ዘልቆበታል። በትምህርቱ ፈጣን የነበረው ተመስገን በዘመናዊ ትምህርትም ጉብዝናው ጎልቶ ወጥቷል። ከጎጃም አዲስ አበባ በመምጣትም በስዊድን ሚሽን ትምህርት ቤት ትምህርቱን ተከታትሏል። በዘመኑ ከነበሩ ጎበዝ ተማሪዎችም አንዱ ነበር።

በ1920ዎቹ የጣሊያን ዳግም ወረራ እንደማይቀርልን በመረዳቱም ህዝብ በተሰበሰበበት ለጦርነት እንዘጋጅ ከማለት አልሰነፈም። ተመስገን በጋዜጠኝነት ሙያ ከማገልገሉም በተጨማሪ በሌሎች መስሪያ ቤቶች አገልግሏል። የኤርትራ ድምጽ የተሰኘ ጋዜጣም ዋና አዘጋጅ ነበር።

በየካቲት 12/1929 ጭፍጨፋ ዋነኛ ተፈላጊ የሆነው ተመስገን ገብሬ በጣሊያኖች እጅ ቢወድቅም ስሙን ሸሸጋቸው። ‘እኔ ተመስገን ገብሬን አውቀዋለሁ፤ አብሬያችሁ ብፈልግ እናገኘዋለን።’ በማለቱም ጣሊያኖቹ አምነውት ከተመስገን ጋር ተመስገንን ይፈልጉ ያዙ። ግና ኋላ በርሱም ላይ የሞት ፍርድ ተፈርዶበት ከተጨፍጫፊዎች መካከል ተገኘ። በጅምላ ጭፍጨፋው መሃል ተመስገን ከመሞት ተረፈ። የጅማላ ጭፍጨፋውን ግን ከመሃሉ ተገኝቶ አይቷል።

ከሞት የተረፈው ተመስገን ወደ ሱዳን ተሰደደ። በዚያም ከአርበኞች ጋር ዋነኛው የትግል አቀጣጣይ ሆነ። ከጣሊያን ሽንፈት በኋላ ወደ ኢትዮጵያ የመጣው ተመስገን ገብሬ የኤርትራ ድምጽ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ በመሆን አገልግሏል። በ1941 ደግሞ በኢትዮጵያ የታተመ የመጀመሪያው አጭር ልቦለድ የሆነው የጉለሌው ሰካራም ልቦለድን አሳተመ።ከጉለሌው ሰካራም በፊት ግን ‘የካቲት 12’ እና ‘ሊቀ ጠበብቱ’ የተሰኙ ልቦለዶችን በጋዜጣ አውጥቷል። ህይወቴ ሲልም ግለ ታሪኩን የጻፈው ደራሲ እና አርበኛ ተመስገን ገብሬ በ1941 አርፏል።

በአብርሃም በለጠ
2022-05-23