ሀገሬ ቲቪ

ዘመናዊ ቴክኖሎጂን መጠቀም የጀመረው ሸገር ቁጠባ እና ብድር ተቋም

በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት ውስጥ የቁጠባ እና ብድር ኅብረት ስራ ማህበራት ያላቸው ሚና እንዲህ በቀላሉ የሚታይ አይደለም። በተለይ መካከለኛ እና አነስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች የጠቃሚ ከማድረግ ረገድ የማይተካ ድርሻ አላቸው።

ባሳለፍነው ዓመት ይፋ በተደረገ የፌደራል ኅብረት ስራ ማህበራት ኤጀንሲ ሪፖፕርት ላይ እንደተመለከተው። ከ92 ሺሕ በላይ መሰረታዊ የሆኑ ማህበራት ይገኛሉ። ታዲያ እነዚህ ተቋማት ግዜውን እና ዓለም ያለበትን ሁኔታ የዋጁ እንዲሆኑ ይጠበቃል።

በዘርፉ ከሚገኙ ተቋማት ውስጥ ሸገር የቁጠባ እና ብድር ኃላፊነቱ የተወሰነ መሠረታዊ የህብረት ስራ ማህበር አንዱ ነው። ተቋሙ ለአባላቱ እና ተጠቃሚዎቹ ያዘጋጀውን ፖርታል፣ የሞባይል መተግበሪያ እና ዌብ ሳይት ይፋ አድርጓል።

ተቋሙ ይፋ ያደረጋቸው እነዚህ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ለሕብረተሰቡ የሚሰጠውን አገልግሎት በተሻለ ጥራት እና ደረጃ ለመስጠት ግዜው የሚጠይቀውን የቴክኖሎጂ ውጤት መጠቀም አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበት ያዘጋጀው መሆኑን የተቋሙ ዋና ስራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ ፋሲካ ሲሳይ ነግረውናል።

“አሁን ያለንበት ግዜ ግሎባላይዜሽን ያለበት ነው። ቀልጣፋ እና ዘመናዊ አገልግሎትን ማቅረብ የግድ ይላል። ስለዚህ እኛም ይህንን መርጠናል”

ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም በዘርፍፉ ከተሰማሩ በሀገሪቱ ከሚገኙ ተቋማት ቀዳሚ ለመሆን የቻለው ተቋሙ ለተጠቃሚዎቹ ግልጽ እና ተጠያቂነት ያለውን አገልግሎት ለመስጠት ቴክኖሎጂው ያግዘኛል ብሏል።

ተቋሙ ከወረቀት ስራ ተላቆ በዘመናዊ መልኩ አገልግሎቶቹን ለመስጠት የጀመረው እርምጃ የደንበኞችን እንግልትም የሚያስቀር እንደሆነ አቶ ፋሲካ ጨምረው ነግረውናል።

“ከወረቀት ስራ ተላቀን ወደ ዘመንዊ መንገድ መምጣታችን በርካታ ነገሮችን አቅሎልናል። በሌሎች ተመሳሳይ ተቋማት ጋር ብድርን በወብሳይት ወይንም በዘመናዊ መተግበሪያ መስጠት አልተለመደም። እኛ ግን ደንበኞቻችን ባሉበት ሆነው ይህንን አገልግሎት አንዲያገኙ ማድረግ እንችላለን። ይህም በርካታ ምልልሶችን ያቀላል።”

ቴክኖሎጂውን ያበለፀገው ኢቴክ አክሲዮን ማህበር በበኩሉ በፋይናንሱ ዘርፍ ላይ ያሉ የቴክኖሎጂ ክፍተቶችን ለመድፈን በማደርገው ጥረት ውስጥ ሸገር የቁጠባ እና ብድር ተቋም ትልቅ እድልን ሰጥቶኛል ብሏል።

በኢቴክ አክሲዮን ማህበር የቢዝነስ ዴቨሎፕመንት ኦፊሰር የሆኑት አቶ እስጢፋኖስ ብርሃኑ ይህንን ብለውናል።

“የፋይናንስ ዘርፉን ማገዝ እንፈልጋለን። ወደ ኮር ባንኪንግ አገልግሎቶቻችንን ማሳደግ እንፈልጋለን። ይህንን ለማድረግ ስናስብ ሸገር ቁጠባ እና ብድር መልካም አጋጣሚን ፈጥሮልናል።”

በዘርፉ የተሰማሩ ተቋማት እንዲህ ያለውን ዘመናዊ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ሊጠቀሙ ይገባል ያሉት ደግሞ የአዲስ አበባ ኅብረት ሥራ ማህበራት ኤጀንሲ የማእራጃ እና ማስፋፊያ ብድን መሪ የሆኑት አቶ ተሰማ ናቸው።

“ሁሉም ተቋማት ዘመኑ የሚፈቅደውን የቴክኖሎጂ ውጤት መጠቀም አለባቸው። የቴክኖሎጂ ውጤቶችን መጠቀሙ የተገልጋዮቻቸውን ድካም ይቀንሳል”

ሸገር ቁጠባ እና ብድር ተቋም በ2013 ዓ.ም በ169 አባላት፣ 1.6 ሚሊዮን ብር ካፒታል የተመሰረተ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት የተመሰረተ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት የአባላቱን ቁጥር ከ1,400 በላይ እንዲሁም ጠቅላላ የሀብት መጠኑም ከ32 ሚሊዮን ብር በላይ ማድረስ ችሏል።

በሳምሶን ገድሉ
2022-05-23