ሀገሬ ቲቪ

ከነብር ጋር የተፋለመችው እናት

ዓለም ቦታዎችን ለሁለት በመክፈል ውጪውን ለሰው ዱሩን ደሞ ለእንስሳ ሰጥታ እያኖረች ነው ።

ታዲያ እግር መርቶን አልያም በ አንድ ጉዳይ ወደ አውሬዎቹ መኖሪያ ካቀናን ከ ቁጡዎቹ እንሣት ጋር ጠብ መፈጠሩ አይቀሬ ነው ።

አሁን የሆነው ግን በተቃራኒ ነው ቁጡው የዱር እንስሳ ቤቱን ጥሎ ወደ ሰዎች መንደር ተገኝቷል ። ነገሩ እንዲ ነው በህንድ ማድያ ፕራዴሽ ግዛት ከባዲ ጂሪያ ጎሳ መንደር የምትኖር ኪራን ባይጋ የተባለች ሴት ከሶስት ልጆቿ ጋር ከጎጆዋ ፊትለፊት ተቀምጣ የሆድ የሆዳቸውን ያወጋሉ ።

ታዲያ ኪራን እና ሶስት ልጆቿ ከዱር አጠገብ ባለው ቤታቸው ተቀምጠው ሳለ የ እለት ጉርሱን ለመፈልግ ከወጣ ነብር ጋር ፊትለፊት ይገጣጠማሉ።

ነብሩም በፍጥነት በመንደርደር ከልጆቿ መሀከል አንድዋን በመንጋጋው በመያዝ ወደ ወጣበት ሳንጃይ ጋንዲ ብሄራዊ ፓርክ ይሮጣል ።

በዚህ የተደናገጠችው እናት በ እጅዋ የያዘችውን ጨቅላ ልጅ በማስቀመጥ ኡ ኡታን እያሰማች ነብሩን መከተል ጀመረች ። ተስፋ ያልቆረጠችው እናት አንድ ማይል ያህል ርቀት ነብሩን በመከተል ካረፈበት ቦታ ትደርሳለች ።

ከአልችል ባይ የእናት አንጀት ውጪ ምንም ያልታጠቀችው ኪራን ልጅዋን በባዶ እጆቿ ከነብሩ ጥፍር ለማላቃቅ የሞት ሽረት ተጋድሎ ታደርጋለች ።

ታዲያ በከፍተኛ የእናትነት መንፈስ በመታገዝ የታገለችው ደፋሯ ሴት በመጨረሻም ልጅዋን ከነብሩ ጥፍር በማላቀቅ በ እቅፏ አደረገች ።

ይሁን እንጂ ነብሩ በቀላሉ ያገኘውን ሲሳይ መልቀቅ አልፈለገም እና ልጅዋን በመለቀቅ እናትየዋን ማጥቃት ጀመረ። ታዲያ ኪራን ልጅዋን ከነብሩ ለማዳን በምትሞክርበት ሰዐት እርዱኝ የሚል ድምጽ ስታሰማ ነበርና ይህን ድምጽ ተከትለው በቦታው የደረሱ ሰዎች እናትየዋን ከ ነብሩ መንጋጋ ማዳን ችለዋል ።

ኪራን የስድስት አመት ልጇን ከነብሩ ለመከላከል ባደረገችው ጥረት ህይወትዋ ባያልፍም ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባት ነበር እና ነብስ አዳኞቹ ከልጅዋ ጋር ወደ ሆስፒታል እንደወሰድዋት ጃግራን ኢንግሊሽ ዘግብዋል ።

በሳንጃይ ጋንዲ ብሔራዊ ፓርክ አቅራቢያ የሚኖሩ የጎሳ ተወላጆች በዱር አራዊት የሚሰነዘሩባቸው ጥቃቶች በጣም ተደጋጋሚ መሆናቸውን ይናገራሉ።

የመንደሩ ነዋሪዎች እናትየዋ ያደረገችውን ታላቅ ተጋድሎ ቢያደንቁም ነገር ገን ዛሬም ለህይወታችን ምንም ዋስትና የለንም እና መላ ሊባልልን ይገባል ሲሉ መለዕክታቸውን አስተላልፈዋል ።

በሳምሶን ገድሉ
2022-05-23