ሀገሬ ቲቪ

400 የቀዶ ህክምና ባለሙያዎችን ያቀፈው ማህበር

የኢትዮጵያ ቀዶ ህክምና ማህበር በጥቂት ባለሙያዎች ተመስርቶ አሁን ላይ 400 የሚደርሱ የቀዶ ህክምና ባለሙያዎችን በአባልነት ይዟል ተባለ።

ይህን ያሉት የማህበሩ ፕሬዝዳንት የሆኑት ዶ/ር አታክልቲ ባራኪ ለሀገሬ ቴቪ ነው።

ከተመሰረተ 26 አመታት የሆኑት ማህበሩ አሁን ላይ በመላ ሃገሪቱ ስምንት ቅርንጫፎች ያሉት ሲሆን የቀዶ ህክምና ባለሙያዎቹን አቅም ለማሳደግ እየሰራ ነው ተብሏል።

በኢትዮጵያ የቀዶ ህክምና ባለሙያዎች ቁጥር አነስተኛ ስለመሆኑ ጥናቶች ይጠቁማሉ።

በጥቂት ባለሙያዎች የተመሰረተው የኢትዮጵያ ቀዶ ህክምና ማህበር አሁን ላይ በመላ ሃገሪቱ የሚገኙ የቀዶ ህክምና ባለሙያዎችን በአባልነት ይዟል። የማህበሩ ፕሬዝዳንት የሆኑት ዶ/ር አታክልቲ ባራኪ ለሃገሬ ቴ.ቪ ማህበሩ ከተመሰረተ 26 አመታት መቆጠራቸውን ገልጸው የባለሙያዎቹን መብት ከማስከበር ጀመሮ የሙያ ብቃታቸውን ለማሳደግ ስልጠና እንዲያገኙ እንደሚሰራ ነግረውናል።

“በሃገሪቱ ደንብ መሰረት የአባላቱን መብት ማስከበር ነው፤ በሁለተኛ ደረጃ የሚሰራው ስራ የባለሙያዎችን የአቅም ደረጃ ማጎልበት ነው። በክህሎትም ሆነ በእውቀት እንዲጨምሩ ማድረግ ነው።’’

ማህበሩ ባለሙያዎቹ የርስ በርስ ግንኙነት እንዲኖራቸው እንደሚያግዝ የጠቀሱት ፕሬዝዳንቱ በጤናው ዘርፍ የሚወጡ ፖሊሲዎች ላይ የማህበሩ አባላት የራሳቸውን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱም ገልጸዋል።

የቀዶ ህክምና ሙያን ለማሳደግ መንግስታዊ እና መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጋር በትብብር መስራት ይገባል ያሉት የማህበሩ ፕሬዝዳንት ማህበሩ ከጤና ሚኒስተር ጋር በጋራ እንደሚሰራም ጠቁመዋል።

የማህበሩ ዋና ጸሃፊ የሆኑት ዶ/ር ዉለታው ጫኔ በጥቂት አባላት የተመሰረተው ማህበሩ አሁን ላይ በመላ ሃገሪቱ ቅርንጫፎቹ በመስፋታቸው ተጨማሪ ማእከላት አስፈልገውታል ብለውናል።

“አሁን ግን በጣም እየሰፋ ስለመጣ በፊት ጠቅላላ ጉባኤዎች ሲኖሩን አዲስ አበባ ብቻ ነበር የምንገናኘው አሁን ግን በየአቅጣጫው ‘ቻፕተር ‘ (ቅርንጫፍ ማእከላት) ከፍተን እየሰራን ነው።”

ዶ/ር ዉለታው ማህበሩ ለተገልጋዮች የተሻለ አገልግሎት መስጠት እንዲቻል የባለሙያዎችን አቅም ማሳደግ ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚሰራ ነግረውናል።

ዶ/ር ዉለታው ከአባላቱ የዩኒቨርሲቲ መምህራን ጭምር ስላሉበት ለሰልጣኝ ተማሪዎች የሚኖረው ትምህርት የተሻለ እንዲሆን እንደሚያግዝም ገልጸዋል።

የማህበሩ ፕሬዝዳንት ዶ/ር አታክልቲ ማህበሩ አባላቱ እንዲሁም የውጭ ዜጎች ስልጠና እንዲያገኙ ኮኤሳ ከተሰኘ የአፍሪካ ተቋም ጋር በጋራ እንደሚሰራም ነግረውናል።

ማህበሩ በስምንት ያክል ቅርንጫፎቹ ከ350 እስከ 400 የሚደርሱ አባላት ያሉት ሲሆን የቀዶ ህክምና ባለሙያዎችን ይበልጥ በማህበሩ ለማቀፍ እየሰራ ነው ያሉን ዶ/ር አታክልቲ ማህበሩ ለሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ወጭዎቹ በማህበሩ አባላት መዋጮ እና በአጋር ድርጂቶች ድጋፍ እንደሚሸፈን ገልጸውልናል።

በአብርሃም በለጠ
2022-05-24