ብዙ ጊዜ የጎሪጥ የሚተያዩ እና በብዙ ጉዳዮች ጠንከር ባለ የቃላት ምልልስ የሚታወቁ ሁለት ሀያላን ሀገራት አሉ። ቻይና እና አሜሪካ። በሚከተሉት የፖለቲካ ርዕዮተ_ዓለም ሆነ በሚያራምዱት የተቃረነ ፖለቲካ አጀንዳ ሁለቱ ሀገራት ብዙ ጊዜ ስማቸው ይነሳል።
ዛሬም ታዲያ እነዚሁ ሀገራት በቃላት መወራረፉን ተያይዘውታል ይለናል የፕረስ ቲቪ ዘገባ። የአሜሪካው ፐሬዝዳንት ጆ ባይደን ራሷን በሯሷ የምታስተዳድረውን ታይዋንን ከቻይና ጥቃት ለመከላከል ወታደራዊ ድጋፍ እናደርጋለን ማለታቸው ቻይናን አስቆጥቷል።
ዋሽንግተን፣ ቻይና በታይዋን ላይ ጥቃት በሚሰነዝርበት ጊዜ ወታደራዊ ጣልቃ መግባቷን ወይም አለማድረጓን በተመለከተ ሲብላላ የቆየ የረዥም ጊዜ ፖሊሲ እንዳላት ይነገራል።
የቻይና ግዛት ምክር ቤት የታይዋን ጉዳይ ጽ/ቤት በትላንተናው ዕለት አሜሪካ “ቻይናን ለመያዝ የታይዋን ካርድ” ትጠቀማለች ሲል ከሷታል።
ዋሽንገተን ቀደም ሲል በሁለቱ ሀገራት መካከል የተመሰረቱትን መርሆች የሚጥሱ ማንኛውንም አስተያየቶችን ወይም ድርጊቶችን ከማድረግ እንድትቆጠብ የጽህፈት ቤቱ ቃል አቀባይ የሆኑት ዙ ፌንግሊያን አሳስበዋልስለዚህም አሜሪካ እየጨራሽ ባለሽው እሳት አንቺም ልትቃጠይ ትችያለሽ እና አደብ ግዢ ስይል ቻይና ለአሜሪካ ቀጠን ያለ መልዕክቷን ልካለች።
የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዋንግዌንቢን በጉዳዩ ላይ ለአሜሪካ በሰጡት ምላሽ በሀገራችን ጉዳይ የማንንም ጣልቃ ገብነት አንሻም፤ የታይዋን ጉዳይ የኛው የውስጥ ጉዳይ ነው ብለዋል።
“የታይዋን ጉዳይ በግልጽ የቻይና የውስጥ ጉዳይ ነው። ስለዚህም ምንም ዓይነት የውጪ ጣልቃ ገብነት አያስፈልገውም።የቻይናን ዋና ፍላጎት የሚመለከቱ እንደ ነጻ ግዛት እንዲሁም ውህደትን የተመለከቱ ጉዳዮች በቀላሉ የምንመለከተው አሊያም ችላ የምንለው ጉዳይ አይደልም”
23 ሚሊዮን ነዋሪዎችን የያዘችው እና ከደቡብ ምስራቅ ቻይና የባህር ዳርቻ 100 ማይል ርቀት ላይ የምትገኝ ደሴቷ ታይዋን በአንድወቅት የቻይና አካል እንደነበረች ታሪክ ያስረዳል።
ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ግን በቻይና በነበሩት የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል በነበረው የእርስበእርስ ጦርነት ታይዋን ከቻይና ልትገነጠል ችላለች።
ታይዋን የራሷን ሕገ መንግስት ያረቀቀች፣በዲሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጡ መሪዎች ያሏት እና ራሷን እንደ አንድ ነጻ ሀገር የምትቆጥር ናት። ይኽን ነጻነቷን 13 ሀገራት አጽድቀውላታል።
ቻይና ታዲያ ሌሎች ሀገራት ለታይዋን እውቅና እንዳይሰጡ ወይም እውቅናን የሚያመለክት ማንኛውንም ነገር ከማድረግ እንዲቆጠቡ ከፍተኛ ዲፕሎማሲያዊ ጫና ታደርጋለች።
ይኹንና ቻይና እኔ ቆሜ ታይዋን ከእኔ ተገንጥላ መቆየቷን ማየት አልሻም ባይ ናት ። በተደጋጋሚ ታይዋን በጄ መግባቷ የማይቀር ነው ስትል ዝታለች።
አሁንም ቢሆን የቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ ከታይዋን ጋር ውህደት መፈጸማችን የማይቀር ነው ብለዋል። ይኽ ውህደት ግን በስምምነት ይኹን በጦርነት ዢ ጂንፒንግ የገለጹት ነገር የለም። ነገር ግን ቻይና ወታደራዊ ባልሆኑ መንገዶች ማለትም ኢኮኖሚያዊ ግንኙነቶችን በማጠናከር እንደገና ለመዋሃድ ልትሞክር ትችላለች የሚል መላ ምት አለ።
አንዳንድ ምዕራባውያን የፖለቲካ ተንታኞች ቻይና እና የታይዋንን ጦርነት ውስጥ ቢገቡ ለታይዋን መሳሪያ የምትሸጠው አሜሪካ ለታይዋን ድጋፍ ሰጪ መሆና እሙን ነው ሲሉ ይናገራሉ።
በሙሉጌታ በላይ
2022-05-24
