ሀገሬ ቲቪ

የጅቡቲ የፈሳሽ ወደብ ግንባታ መቀላጠፍ

በጅቡቲ በዓመት 13 ሚሊየን ቶን ገቢ እና ወጪ ፈሳሽ ጭነት የሚያስተናግደው ወደብ ግንባታ ከግማሽ ደረሰ፡፡ ጅቡቲ እየገነባች የሚገኘው የዳመርጆግ ፈሳሽ ጭነት ወደብ ስራ ከግማሽ በላይ መከናወኑ ተሰምቷል፡፡ በርካታ የሎጅስቲክ ማስፋፊ እና አዳዲስ ግንባታዎች እያከናወነች የምትገኘው ጅቡቲ ከምትገነባቸው አዳዲስ አገልግሎት መስጫዎች መካከል የዳመርጆግ የፈሳሽ ጭነት ማስተኛገጃ ወደብ ይገኝበታል፡፡ ግንባታው ሶማግ ለተባለ በዘርፉ ከፍተኛ ልምድ ላለው የሞሮኮ ኩባንያ ባለፈው ዓመት መስከረም ላይ መሰጠቱ አይዘነጋም፡ የዳመርጆግ ፕሮጀክት በዋናነት ነዳጅ ለማስተናገድ ታልሞ በፍጥነት እየተሰራ ያለ ወደብ ነው፡፡ የዳመርጆግ የፈሳሽ ጭነት ማስተኛገጃ ወደብ ዋና ስራ አስፈፃሚ ሃሰን አህመድ እንደገለጹት የግንባታው ስራ በሦስት ምእራፍ ተከፍሎ በአምስት ዓመት እንደሚጠናቀቅ ተገምቶ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ በጥሩ ሁኔታ እየተከናወነ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ከታቀደለት ጊዜ ቀድም ብሎ ሊጠናቀቅ እንደሚችል ተገምቷል፡፡ ወደቡ በአንድ ጊዜ 2 መርከቦች መቀበል የሚችል ሲሆን በዓመት 13 ሚሊየን ቶን ገቢ እና ወጪ ፈሳሽ ጭነት ያስተናግዳል፡፡

በሀገሬ ቴቪ
2021-12-09