የዛሬው እለቱን ከታሪክ ቤተ እስራኤላውያን ጋር ወደ ተያያዘ ታሪክ ይወስደናል። ወደ 1983። ኢትዮጵያ ትልቅ ፖለቲካዊ አለመረጋጋት ውስጥ በነበረችበት በእስራኤል የተከናወነው ኦፕሬሽን ሰለሞንን እንቃኛለን። በዚህ የእስራኤል ወታደራዊ ተልእኮ በሆነው ኦፕሬሽን ሰለሞን ከ14 ሺህ 200 በላይ ቤተ እስራኤላውያን በ36 ሰአታት በረራዎች ከኢትዮጵያ ወደ እስራኤል እንዲጓዙ ተደርጓል።
በ1983 የደርግ መንግስት ስልጣኑን አጥቷል። ኢትዮጵያ ባሳለፈችው ጦርነት የተነሳ መረጋጋትን አላገኘችም። በዚህ በኩል ደግሞ እስራኤል ወደ ተስፋይቱ ምድር የመሄድ ፍላጎት የነበራቸውን ቤተ እስራኤላውያንን ወደ እስራኤል የመውሰድ እቅድ ወጥናለች። ኦፕሬሽን ሰለሞን። በዛሬዋ እለት ከ31 አመታት በፊት የተከናወነ ክስተት።
ከኦፕሬሽን ሰለሞን አስቀድሞ ግን በኦፕሬሽን ሙሴ እና በኦፕሬሽን ኢያሱ ቤተ እስራኤላውያን ከኢትዮጵያ ወደ እስራኤል እንዲሄዱ ተደርጓል።
የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ አለመረጋጋትን በመመልከት የእስራኤል መንግስት እና መከላከያ ሃይል ቤተ እስራኤላውያንን ከኢትዮጵያ የማስወጣት እቅድ ወጠኑ። በኦፕሬሽን ሰለሞን በአሜሪካ ለኢትዮጵያ አይሁዶች የተሰኘ ማህበር ቤተ እስራኤላውያን አደጋ ላይ ናቸው የሚል ግፊት በመፍጠራቸው አሜሪካም ተሳታፊ ነበረች።
የደርግ መንግስት ለቤተ እስራኤላውያን ወደ እስራኤል መጓዝ እንዲችሉ መፍቀድ ጋር ተያይዞ አሜሪካ ቀደም ባሉት ሁለት ተልእኮዎችም ተሳትፎ ነበራት።
ኦፕሬሽን ሰለሞንን የወቅቱ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስተር ይስሃቅ ሻሚር ይቆጣጠሩት ነበር። ይሄው ምስጢራዊ ወታደራዊ ተልእኮ በየአሜሪካ ማህበር ለኢትዮጵያ አይሁዶች ከፍተኛ እርዳታ እንዲፋጠን ሆኗል።
ቤተ እስራኤላውያንን ከኢትዮጵያ የማውጣት እቅዱ በእስራኤል መንግስት በሂደት እንዲሆን የታሰበ ነበር። የሃገራችን የወቅቱ ሁኔታ ግን ነገሩ በፍጥነት እንዲከናወን የአሜሪካ ማህበር ለኢትዮጵያ አይሁዶች ግፊት ማድረጉ አልቀረም።
ቤተ እስራኤላውያን ከጎንደር ዙሪያ ወደ አዲስ አበባ በባስ፣ በፈረስ እና በእግር መጓዛቸው የግድ ሆነ። በዚህ ተልእኮ 36 የእስራኤል አየር ሃይል ጃምቦ ጀቶች እና በመቶዎች የሚቆጠሩ ወታደሮች ተሳታፊ ሆነዋል። በተለያየ መንገድ ወደ አዲስ አበባ እንዲደርሱ የተደረጉት ቤተ እስራኤላውያንን ለማጓጓዝ 35 አውሮፕላኖች ይጠብቋቸዋል።
ብዙ ተጓዦችን መያዝ እንዲቻልም አውሮፕላኖቹ ወንበር እንዳይኖራቸው ተደረጓል። አንድ አውሮፕላን ከ 1000 በላይ ተጓዦች እንዲይዝ ተደረገ። ይሄው የተጓዦች ብዛት የአለም ሪከርድን መያዝ የቻለ ነው። በዚህ ጉዞ ከ14 ሺህ 200 በላይ ቤተ እስራኤላውያን ወደ እስራኤል መጓዝ ችለዋል። ሁለት ልጆችም በበረራ ላይ ተወልደዋል።
ተልእኮው በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቅ ችሏል። ከሚለብሱት ልብስ የዘለለ ይዘው ለወጡት ቤተ እስራኤላውያን ግን ወደ አዲስ አለም የመቀላቀል ጅማሮ ሆነ።
በ36 ሰአታት የተደረገ ተልእኮ ፤ ኦፕሬሽን ሰለሞን።
ቤተ እስራኤላውያንን ከኢትዮጵያ ወደ እስራኤል ለማጓጉዝ የተደረገ የእስራኤል ጦር ተልእኮ ነው። ግንቦት 16 እና 17 1983 በተካሄደው በዚህ ተልእኮ 35 የእስራኤል አውሮፕላኖች ያለማቋረጥ በረራዎችን በማድረግ በ36 ሰአታት ውስጥ 14 ሺህ 325 ቤተ እስራኤላውያንን አጓጉዘዋል።
በአብርሃም በለጠ
2022-05-24
