በአንድ ሀገር ውስጥ በህዝብ ተፈቅዶለት አልያም ተመርጦ ሊሆን ይችላል፣ ካልሆነም በጉልበት እኔ አውቅላችኋለው ብሎ፤ ብቻ መንግስት የሚባል አስተዳዳሪ አካል አለ።
ይህ አካል ስራዬን ያቀላጥፉልኛል ያላቸውን ተቋማትን ያደረጃል። እነዚህን ተቋማት የሚመሩለትንም ከጉያው ስር እያወጣ ማዕረጉን ያጎናፅፋቸዋል።
ታዲያ እነዚህ የተቋማት መሪዎች ለተሾሙበት ዓላማ ይረዳናል ያሉትን ሁሉ ያደርጋሉ፣ ይወጣሉ ይወርዳሉ። ይህንን ሁሉ መንደርደራችን አንድ ሚንስትር ተናገሩ የተባለው ነገር በርካቶችን አስገርሟል፤ እኛንም ወይጉድ አሰኝቶናል እና ነው።
ሰውየው የኡጋንዳ የማይክሮ ፋይናንስ ሚንስትር ድኤታ ናቸው። ታዲያ በአንድ መድረክ ላይ ተገኝተው ድሆች መንግስተ ሰማያት አትገቡም እና እርማችሁን አውጡ አሉ።
ሚኒስትር ዴኤታው ሃሩናን ኬዩኔ ካሶሎ ይባላሉ። ድሀ በመሆናችሁ ሳቢያ መንግስተ ሰማያት አምልጣችኋለች ተግታችሁ ሀብታም ሁኑ እያሉ ነው።
ሰውየው ሲናገሩ እንዲህ አሉ "አንዳንዶቻችሁ በመጸለይ ብቻ ወደ መንግስተ ሰማይ እንሄዳለን ብለው ያስቡ ይሆናል ነገር ግን እግዚአብሔር ሁላችንን በአምሳሉ ፈጥሮናል። በአምሳሉ ከፈጠረን እናንተ ድሆች ናችሁ። ለምን ሌሎች ባለጠጎች ሆኑ? ድሀ በመሆን ስላሸማቀቃችሁት እግዚአብሔር ይቀጣችኋል እና ገነት አትገቡም።”
“ተግቶ በመፀለይ ብቻ ወደ መንግሥተ ሰማያት እንገባለን ብለው የሚያስቡ ሊረሱት ይገባል” ሲሉ ተደምጠዋል።
ግለሰቡ ፕሬዚዳንታዊ ሥራ እና ሀብት ፈጠራ ላይ በርከት ብለው ለተእበሰቡት ኡጋንዳውያን እንደተናገሩት ከሆነ በርካታ የሀገራቸው ዜጎች ሀብታም እንዳይሆኑ ሰቅዞ የያዛቸው እርሳቸው ኣጉል ያሉት እሳቤ ባይ ናቸው።
ለምሳሌ አሉ ሰውየው በሰዉ መሀል እየተመልለሱ የሞተር ሳይክል እና የታክሲ ሾፌሮችን ውሰዷቸው። እያንዳንዳቸው በቀን ቢያንስ 5 ሺሕ ሽልንግ ከመእረታዊ የምግብ እና መጠጦች ውጪ ለተጨማሪ ምግብ፣ መጠጥ፣ እና ሌሎች አላስፈላጊ ነገሮች ያባክናሉ ሲሉ የሀገራቸውን ሰዎች ወቅሰዋል።
በአንድ አካባቢ ውስጥ ቢያንስ 2 ሺሕ ያክል የሞተር ሳይክል እና የታክሲ ሾፌሮች አሉ ብንል እና በቀን ከ5ቱ ሺሕ ውስጥ 2 ሺሑን ያህል ቢቆጥቡ በዓመት ከ1.4 ቢሊዮን በላይ ሽልንግ መቆጠብ ይቻላል ሲሉም ምክራቸውን ለግሰዋል።
ታዲያ ባለ አንድ ስራ የሀገራቸውን ወጣቶችንም የመንግስትን እጅ ብቻ መጠበቅ አግባብ አይደለም እና ስራዎችን ያለመታከት ስሩ ብለዋል።
ሰውየው ለኡጋንዳውያን ሆዳችሁንም በመጠኑ አድርጉት ብለዋል። ይህንን ኦዲት ማድረግ ይገባል በርካታ ኡጋንዳውያን ለሆዳቸው ያለአግባብ ወጪዎችን ያበዛሉም ነው ያሉት።
ታዲያ ከድህነት ለመውጣትእና ወደ መንግስተ ሰማያት መሄጃ መንገዳችሁን ለመጥረግ በተጀመሩ የመንግስት ተባራት ላይ ዜጎች በአግባቡ እንዲሳተፉም ጥሪን አቅርበዋል።
በሳምሶን ገድሉ
2022-05-24
