የሰው ልጅ የማወቅ ፍላጎት የገፋቸው በርካታ ግኝቶች በዓለማችን ላይ ወይ ጉድ አሰኝተውናል።
አንዳንዶቹም መጠናታቸው ያለው ሚና ግራ እስኪያጋባ ድረስ በርካቶችን ያነጋግራል።
አሁን የሰማነውን ከየትኛው ትመድቡታላችሁ።
ተመራማሪዎች፤ ዓለም የዲሞክራሲ ተምሳሌት የሆኑ እርግቦችን አግኝታለች እያሉን ነው።
እነዚህ ጥቋቁር የአዕዋፍ ዝርያዎች ጃክዳውስ ይባላሉ።
ጃክዳውሶች በተደረገባቸው ጥናት በድምጻቸው ተግባብተው ውሳኔያቸውን በጋራ ያፀድቃሉም ነው የተባለው።
ታዲያ ይህ የአዕዋፍቱ ነገር በሰዎች ዓለም ውስጥ ካለው ፓርላማ ጋር ተመሳሳይ ነውም ብለዋል ተመራማሪዎቹ።
በርከት ብለው በአንድ ቦታ ላይ በመስፈር እና ሁሉም በአንድ ላይ ተነስተው በመብረር የሚታወቁት እነዚህ ዝርያዎች በርካቶች ይደመሙባቸዋል።
ተመራማሪዎቹ እንደሚሉት ከሆነ ታዲያ እነዚህ ፍጡራን በአንድ ላይ ተነስተው ከመብረራቸው አስቀድመው ለሰዎች በማይገባ የራሳቸው ጩኸት ድምፀ ውሳኔ ያደርጋሉ።
እነዚህ የወፍ ዝርያዎች በርከት ብለው በሚገኙባቸው ቦታዎች ላይ በተደረገ ጥናት አዕዋፍቱ ለበረራ ከመነሳታቸው በፊት በተመሳሳይ የድምጽ አወጣጥ ይነጋገራሉ።
እነዚህ ድምፆች የቡድን ውሳኔን ለማሳለፍ የሚጠቀሙባቸው ናቸው።
እንደ ተመራማሪዎቹ ከሆነ አንደኛው ጃክዳውስ ቦታውን ለቆ መሄድ ሲፈልግ ለየት ያለ ድምጽ ያውጣል።
በቦታው የሚገኙት ሁሉም አዕዋፍት በሀሳቡ ሲስማሙ በጋራ ተነስተው መብረር ይጀምራሉ።
የጥናት ቡድኑ መሪ እንዳሉት ከሆነ እንዲህ ያሉ ጥናቶች እምብዛም የተለመዱ አይደሉም።
በርከት ያሉ እንስሳት በጋራ የሚከውኗቸውን ተግባራት ለመከወን እንዴት እንደሚቀናጁ ለማወቅ የበለጠ እድልን ይፈጥራል ተብሏል።
በሳምሶን ገድሉ
2022-05-25
