ሀገሬ ቲቪ

ቻይና ሩሲያ የጋራ የጦር ልምምድ አንድምታ

ሞስኮ ወታደራዊ ዘመቻውን በምስራቅ ዩክሬን ከጀመረች በኋላ ቻይና እና ሩሲያ የመጀመሪያውን ወታደራዊ ልምምድ አድርገዋል። የጦር ልምምዱ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ወደ ክልሉ ጉብኝት ማድረጋቸውን ተከትሎ መሆኑ ደግሞ ሁለቱ ሀገራት ያሰቡት ነገር ይኖር ይሆን የሚል ያልተመለሰ ጥያቄን አስከትሏል።

የቻይና መከላከያ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው ከሆነ የጦር ልምምዱ የተደረገው በመዕራብ ፓሲፊክ ወይም ቻይና እና ጃፓን በሚዋሰኑበት አካባቢ መሆኑን አስታውቋል።ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አክሎም ልምምዱ የሁለቱ ሀገራት ዓመታዊ ወታደራዊ ትብብር እቅድ አካል ነው ብሏል።

የሁለቱን ሀገራት የጦር ልምምድ ጃፓን በጦር ሚኒስትሯ በኩል አውግዛለች። ጭራሹኑ ተቀባይነት የሌለው እና ጸብ አጫሪ ነው ስትል ልምምዱን በጽኑ ኮንናለች።

ልምምዱ የተካሄደው ጃፓን የኳድሪተራል ቡድን አሊያም የአራትዮሽ የደኀንነት ውይይት እያስተነገደች ባለበት ወቅት ነው። አሜሪካ፣ ጃፓን፣ህንድ፣አውስትራሊያ ደግሞ የቡድኑ አባል ናቸው።

በአጭር ስሙ ኳድ የሚባለው ቡድን በጃፓን ስብሰባ በተቀመጠበት ወቅት ቻይና እና ሩሲያ ልምምዱን ማድረጋቸው በግድ ጦርነት እንፈልጋለን እያሉን ነው ብላለች ጃፓን። አሜሪካ የምትመራው ይኽው ቡድን በኢንዶ ፓሲፊክ ክልል የቻይናን ጫና ለመከላከል በደበኛ ባልሆነ መንገድ የተፈጠረ ስብስብ እንደሆነ ይነገራል።

ቻይና እና ሩሲያ ከሶስት ዓመት በፊት ተመሳሳይ የጦር ልምምድ አድርገው ነበር። የአሁኑ የአየር ላይ በረራ ከጃፓን ባህር እስከ በፊሊፒንስ ባህር አናት ያንዣንበበ ልምምድ ነበር። ሩሲያ ታዲያ ያደረግነው የ13 ሰዐት የአየር በረራ "በአለም አቀፍ ህግ በተደነገገው መሰረት ነው" ማንም ላይ አልደረስንም ብላለች።

ሩሲያ ይኽን ትበል እንጂ ደቡብ ኮሪያ ሁለት የቻይና አራት የሩሲያ ባጠቃላይ ስድስት የጦር አውሮፕላኖች ወደ እኔ አየር ክልል ጎራ ብለው ነበር ስትል ክልምምዱ በኋላ ባወጣችው መግለጫ አስታውቃለች።

በዩክሬን ለሶስት ወራት የዘለቀው ጦርነት በሺዎች የሚቆጠሩ ሲቪሎች ሲሞቱ በቻይና እና በሩሲያ መካከል ያለው አጋርነት እንዳልተዳከመ በሀገራቱ መሀከል የተደረገው ወታደራዊ እንቅስቃሴው ትልቅ ማሳያ ነበር ሲል ዘኒዎርክ ታይምስ ጽፏል። የአሜሪካ ባለሥልጣናት በበኩላቸው የቻይና የባህር ኃይል መርከቦች በጋራ ልምምድ ላይ እንደተሳተፉ የሚያሳይ ማስረጃ እንዳላቸው ተናግረዋል።

ሩስያ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሰርጌ ላቭሮቭ ሰኞ እለት እንደተናገሩት ሞስኮ ከቻይና ጋር ያላትን ግንኙነት ለማሳደግ በትኩረት እንደምትሰራ ተናግረው ነበር።

“አሁን ምዕራባውያን 'የአምባገነን አቋም' ስለያዙ ከቻይና ጋር ያለን ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት በፍጥነት ያድጋል” ብለዋል ላቭሮቭ።

በሙሉጌታ በላይ
2022-05-25