ሀገሬ ቲቪ

የኢትዮጵያ የቦይንግ አውሮፕላን ግዢ

የኢትዮጵያ አየር መንገድ አምስት ተጨማሪ ቦይንግ 777 የዕቃ ጫኝ አውሮፕላኖች ሊገዛ ነው፡፡ ግዢው የቦይንግ የዕቃ ጫኝ አውሮፕላኖቹን ቁጥር ለማሳደግ ዓላማ አድርጓል፡፡

አየር መንገዱ ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው ለመግዛት ያዘዛቸው አምስቱ አውሮፕላኖች የቅርብ ጊዜ እና ዘመናዊ የዕቃ ጫኝ አውሮፕላኖች ናቸው፡፡

ከቀድሞዎቹ ጋር ሲነፃፀርም ከ17 በመቶ ያነሰ ነዳጅ የሚጠቀም እና አነስተኛ የበካይ ጋዝ ልቀትን መያዝ ይችላል ተብሏል፡፡ በአሁኑ ሰዓት በገበያው ላይ መሪ የሆነው ቦይንግ 777 የዕቃ ጫኝ አውሮፕላን የዓለማችን ግዙፉ እና ረጅም ርቀት መጓዝ የሚችል ባለሁለት ሞተር አውሮፕላን መሆኑን አየር መንገዱ ገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአሁኑ ሰዓት ዘጠኝ ቦይንግ 777 የዕቃ ጫኝ አውሮፕላኖች አሉት፡፡

በፍሬህይወት ታደሰ
2022-05-26