በዓለም ላይ በገዳይነታቸዉ ከሚታወቁት የካንሰር አይነቶች የሴቶችን የመራቢያ ክፍል የሚያጠቃዉ የማህፀን ጫፍ ካንሰር አንዱ ነዉ። በሽታው ሂውማን ፓፒሎማ በተሰኘ ቫይረስ የሚመጣ ሲሆን ዋነኛ መተላለፊያው የግብረ ስጋ ግንኙነት ነው።
በኢትዮጵያም በገዳይነቱ በሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ነዉ።ይህ የካንሰር በሽታ የገዳይነቱን ያህልም ቀድሞ መከላለክልና ማዳን የሚቻል በመሆኑ በሽታዉን ለመከላከል ከሚደረግ ጥንቃቄ ጎን ለጎን የግብረ ስጋ ግንኙነት የጀመረች ሴት በዓመት አንድ ጊዜ ቅድመ ምርመራ እንድታደርግ የህክምና ባለሙያዎች ይመከራሉ።
በሽታዉን ለመከላከል የሚያስችል ክትባት መዉሰድም በባለሙያዎች የሚመከር ሌላኛዉ መንገድ ነዉ። በሽታውን የበለጠ አስከፊ ያደረገው 80 በመቶ የሚሆነው ከ10 እስከ 20 ዓመት ድረስ ምልክት ሳያሳይ መቆየቱ እንደሆነ ይነገራል።
ዶ/ር ትዕዛዙ አለሙ በአዲስ ህይወት ሆስፒታል የማህጸን በር ጫፍ ካንሰር ባለሙያ ናቸው። በሽታዉን ቀድሞ ለመከላከል የሚያስችል ግንዛቤና መረጃ እጦት እንዲሁም የመከላከያ ክትባት አለማግኘት በሽታውን እያባባሰው ነው ብለውናል።
ባለሙያው እንደ ሀገር የማህጽን በር ጫፍ ካንሰር ወይም «ሰርቪካል ካንሰር» ን ለማከም የባለሙያ ዕጥረት እንዲሁም የህክምና ተቋማት እጥረት አለ ባይ ናቸው።
የህክምና ባለሙያው ከአቅመ ሄዋን በፊት ከሚፈፀም የግብረ ስጋ ግንኙነት ራስን በመጠበቅ ና የማህጸን በር ጫፍ ቅድመ ምርመራ በማድረግ በሽታውን መከላከል እንደሚቻል መክረዋል።
በሽታውን ለመለየት ምርመራ የሚያድርጉት ሴቶች 5 በመቶ ብቻ መሆናቸውን ዶ/ር አትኩሬ ደፋር በህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የስርዓተ ጤና ከፍተኛ ተመራማሪ ነግረውናል ።
በአፍሪካ 10 አገራት ብቻ ናቸው የማህጻን በር ጫፍ ካንሰር ክትባትን ለዜጎቻቸው የሚሰጡት። ከእነዚህም መካከል ኢትዮጵያ አንዷ ተጠቃሽ ሀገር ናት።
የዓለም ጤና ድርጅት ሁሉም ሴቶች አስራ አምስት አመት ሳይሞላቸው ክትባቱን እንዲውስዱ ይመክራል። ዕድሜያቸው 14 ዓመት ለሆኑ ልጃገረዶች በሀገር አቀፍ ደረጃ የማህጸን በር ጫፍ ካንሰር መከላከያ ክትባት በትምህርት ቤቶች፣ በጤና ተቋማትና በሚዘጋጁ ጊዜያዊ የክትባት ማዕከሎች ክትባቱ እየተሰጠ እንደሆነ ጠቁመው በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ሳቢያ ከትግራይ ክልል ውጪ 2 ሚሊዮን ሰዎችን መከተብ መቻሉን ነግረውናል።
በዓለም ላይ በየዓመቱ 528 ሺህ ሴቶችን የሚያጠቃ ሲሆን 270 ሺሕ ያህሉን ደግሞ ለህልፈተ ይዳርጋል። ከዚህም ዉስጥ 85 በመቶ የሚሆነዉ የሞት መጠን እንደ ኢትዮጵያ አይነት በማደግ ላይ ባሉ አገሮች ነው፡፡
በሃገራችን በየዓመቱ ወደ 7 ሺሕ የሚሆኑ ሴቶች በማህጸን በር ጫፍ ካንሰር በሽታ ይያዛሉ፡፡ ከዚህም ዉስጥ 70 በመቶ የሚሆኑት ለመዳን ሳይበቁ ይህችን ዓለም ይሰናበታሉ።
በመቅደስ እንዳለ
2022-05-26
