ዛሬ በእለቱን ከታሪክ ወደ 19ነኛው መቶ ክፍለ ዘመን መለስ ብለን በታሪክ ውስጥ ከስመ ጥሩ ወታደራዊ የጦር ስልት ነዳፊዎች አንዱ የሆነውን ናፖሊዮንን እንዳስሳለን።
ናፖሊዮን የፈረንሳይ የጦር መሪ እና ንጉሰ ነገስት የነበረ ሰው ነው።በዛሬዋ እለት ከ217 ዓመታት በፊት ናፖሊዮን ቦናፓርቴ በሚላን የጣልያን ንጉስ ሆኗል።በታሪክ ውስጥ ታላቅ የጦር ስልት ነዳፊ እንደሆነ የሚነገርለት ናፖሊዮን ቦናፓርቴ የተወለደው በሜዲትራኒያኗ ደሴት ኮርሲካ በፈረንጆቹ 1769 ነው። ናፖሊዮን በ19ነኛው መቶ ክፍለ ዘመን አብዛኛውን የአውሮፓ ክፍል መቆጣጠር የቻለ የፈረንሳይ የጦር መሪ እና ንጉስ ነው።
በፈረንሳይ ወታደራዊ አካድሚ መመረቅ ችሏል። ናፖሊዮን በ18ተኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጨረሻ በፈረንሳይ አብዮት በፍጥነት የውትድርና ማእረግ ማግኘት ችሏል። አውሮፓ የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ በነበረችበት በዚያ ዘመን ፈረንሳይ ከሌላው የአውሮፓ ክፍል ጋር ጦርነት ላይ ነበረች። ሃገሪቱን ከውድቀት ለመመለስና የፈረንሳይ መንግስትን ለመረከብ ናፖሊዮን ከነበረበት የግብጽ ዘመቻ ለመመለስ ተገደደ።
በመፈንቅለ መንግስት ስልጣን በመያዝም ራሱን ንጉሰ ነገስት ብሎ ሾመ። በፈረንጆቹ 1800 ለመጀመሪያ ጊዜ ቆንስል ከሆነ በኋላ ሃይሉን እንደገና በማሰባሰብ ኦስትርያን አሸነፈ። ኋላም የናፖሊዮን ረቂቅ ህግን አወጣ። የፈረንሳይን ግዛት አቋቋመ።
ናፖሊዮን ግዛቱን ማስፋቱን ቀጠለ። ጣሊያን፣ ኦስትሪያ፣ ስፔይን፣ ስዊድን፣ ኖርዌይ እና ሊሎችም የአውሮፓ ሃገራት በናፖሊዮን እና ሰራዊቱ ሽንፈት ገጥሟቸዋል።
በአጠቃላይ በፈረንጆቹ ከ1803 እስከ 1815 ፈረንሳይ በናፖሊዮን ጦርነት ተሳትፋለች። ናፖሊዮን ለቀጣዮቹ የጦርነት ጊዜዎች ዝግጅት አዲስ ነጻ ለወጣችው አሜሪካ በሰሜን አሜሪካ የፈረንሳይ ግዛት የነበረችውን ሊዊዚያና በ15 ሚሊዮን ዶላር ሸጧል። ኋላ ግብይቱ የሊዊዝያና ግብይት ተብሏል።
በ1810ሮቹ ናፖሊዮን ሽንፈት ማስተናገድ ጀመረ። ወደ ሩስያ ሰፊ ዘመቻ አደረገ። ግና ደግሞ ከ600 ሺሕ የናፖሊዮን ዘማች ከሩስያውያን ምህረት የለሽ የመልስ ምት ተርፈው መውጣት የቻሉት 100 ሺሕ ያክሉ ብቻ ናቸው።
ብዙ የአውሮፓ ክፍሎችን መቆጣጠር የቻለው የናፖሊዮን ጦር በየቦታው የህብረት ጥቃት ይደርስበት ጀመር። በሌፕዚግ ጦርነት የናፖሊዮን ጦር በኦስትሪያ፣ ፕሩሽያ፣ ሩስያ እና ስዊድን የህብረት ሃይል ሽንፈት ገጠመው። ናፖሊዮን ወደ ፈረንሳይ አፈገፈገ። ኋላም ጥምር ሃይሎቹ ፓሪስን ያዙ።
በ40ዎቹ መካከል የሚገኘው ናፖሊዮን ዙፋኑን እንዲለቅ ተገደደ። በፎንታይንብለዉ ስምምነት በጣሊያን የባህር ዳርቻ በሜዲትራኒያን ደሴት ወደምትገኘው ኤልባ በግዞት ተወሰደ። በትናንሽ ደሴት ላይ ሉዓላዊነት ተሰጠው ፤ ሚስቱ እና ልጁ ወደ ኦስትሪያ ሄዱ።
አንድ ዓመት ካልሞላ የስደት ጊዜ በኋላ ናፖሊዮን አምልጦ በደጋፊዎች ወደፓሪስ ተመልሶ አዲሱ ንጉስ እንዲሸሹ አደረገ። በ100 ቀናት ዘመቻውም በተናጠል የአውሮፓ ሃይሎችን ማሸነፍ ቢችልም። በህብረት የተከፈተበትን ጥቃት ለመቋቋም ከባድ ሆነበት።
በብራሰልስ አቅራቢያ በዋተርሉ ጦርነት ላይ በእንግሊዝ እና ፕሩሽያ ሃይሎች ትብብር ሽንፈት ገጠመው። በአውሮፓ የጦር ስልት ነዳፊነቱ የሚደነቀው ናፖሊዮን እንደገና ከስልጣን እንዲለቅ ተገደደ።
በፈረንጆቹ 1815 ወደ ሴንት ሄሊና ደሴት በመሰደድም ከአምስት ዓመታት በኋላ በዚያው በ51 ዓመቱ በጨጓራ ካንሰር ዓለምን ተሰናበተ።
በአብርሃም በለጠ
2022-05-26
