ሀገሬ ቲቪ

ዓለም አቀፍ የምጣኔ ሀብት ውድቀት ሊከሰት ይችላል መባል

የዓለም ባንክ የዩክሬን እና የሩሲያ ጦርነት ዓለም አቀፍ የምጣኔሀብት ውድቀት ማስከተሉ የማይቀር ነው ሲል አሳስቧል። በተለይም ሁለቱ ሀገራት በምግብ፣ በኃይል እና በማዳበሪያ ምርቶች የታወቁ እና ወደ ሌሎች ሀገራት በገፍ የሚለኩ በመሆናቸው በዓለም ምጣኔሀብት ላይ ያላቸው ሚና በእጅጉ የጎላ ነው።

በቻይና ያለው ጠበቅ ያለ የእንቅስቃሴ ገድብ እዚህ ላይ ሲጨመር ነገሩን ከድጡ ወደ ማጡ ያደርገዋል ሲሉ የዓለም ባንክ ዋና ኃላፊ ዴቪድማልፓስ ተናግረዋል። ኮቪድ 19ኝን ምክንያት ያደረገው የፋይናንስ ፣የማኑፋክቸሪንግ እና በሻንጋይ ያለው የንግድ መርከብ ማዕከል ቦታዎች የእንቅስቃሴ ገደቦች መጣላቸው በዓለም ምጣኔ ሀብት ላይ የሚያደርሱት ጉዳት ከፍተኛ መሆኑ ተነግሯል ስለዚህም የተዘጉ ኢንዱስትሪዎች ወደ ቀድሞ ሥራቸው እንዲመለሱ ጥሪ አቅርበዋል።

ኃላፊው አክለውም ዓለም አቀፉን የምጣኔሀብት ዕድገት አሊያም ጂዲፒን ስንመለከት ይኽን የምጣኔሀብት ውድቀት መቆጣጠር የሚቻልበት መላ ከባድ ያደርገዋል ሲሉ ተነገረዋል።ጂዲፒው ምን ያህል አሽቆልቁሏል የሚለውን ግን ከመግለጽ ተቆጥበዋል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።

የዓለም ባንክ ባለፈው ወር፣ የዚህ ዓመት የአለም ምጣኔ ሀብት ዕድገት ትንበያውን ወደ 3ነጥብ2 በመቶ ዝቅ አደርጎ ነበር።ከቀናት በፊት የተባበሩት መንግስታት ዋና ጸሓፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በሩሲያ እና በዩክሬን ጦርነት ምክንያት እየተክሰተ ስላለው ዓለም አቀፍ የምግብ ዕጥረት እና ዋጋ መናር በሰጡት መግለጫ ከዚህ ችግር ለመውጣት የሁለቱ ሀገራት ምርት እንደገና ወደ ዓለም አኮኖሚ እንዲቀላቀሉ ማድረግ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

“የዩክሬን ምግብ ምርትን እንዲሁም በሩሲያ እና በቤላሩስ የተመረተውን ምግብ እና ማዳበሪያ ወደ ዓለም ገበያ ሳይቀላቀል በዓለም አቀፍ ደረጃ ለተከሰተው የምግብ ቀውስ ምንም ውጤታማ መፍትሔ ማምጣት አይቻልም”

እንደ ነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝ ያሉ የኃይል ዋጋ በእጥፍ ይጨምራል የሚለው ሀሳብ በራሱ የምጣኔሀብት ውድቀትን ወይም መመሰቃቀልን ለመቀስቀስ በቂ እንደሆነ ነው የዓለም ባንክ ያስታወቀው።

የዓለም ባንክ ኃላፊ ሚስተር ማልፓስ ብዙ የአውሮፓ ሀገራት አሁንም በሩሲያ ላይ በነዳጅ እና በጋዝ ላይ ጥገኛ እንደሆኑ ተናግረዋል። እዚህ ጋር ማስታወስ የሚገባው ጉዳይ ቢኖር የአውሮፓ ኀብረት ሀገራት ከሩሲያ የሚያስገቡትን ነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝ ሙሉ ለሙሉ ለማቆም የስምምነት ውል አስረናል ማለታቸውን ነው። በተለይም ሩሲያ ሩብል በተሰኘው በራሴው መገበያያ ገንዘብ ካልሆነ ነዳጄን አልሸጥም ማለቷን ተከትሎ ብዙ ሀገራት ዐይናቸውን ወደ ሌላ አህጉርና ቀጠና ላይ አድርገዋል።

የአሜሪካው የንግድ ምክር ቤት ባዘጋጀው የበይነመረብ ስብሰባ ዴቪድማልፓስ ሩሲያ በቀጠናው የምታደርገው የጋዝ አቅርቦቶችን የማቋረጡ እርምጃ ከፍተኛ መቀዛቀዝ ሊያስከትል እንደሚችል ተናግረዋል።

በአውሮፓ ከፍተኛ ምጣኔሀብት ባለቤት በሆነችው እና በዓለም አራተኛ ደረጃን በያዘችው ጀርመን ከፍተኛ የኃይል ዋጋ ከወዲሁ ጫና እያሳደረ መሆኑ እንደአብነት ተነስቷል።

የኢኮኖሚ አቅማቸው የፈረጠመ ነው ከሚባሉት ሀገራት በተቃራኒው የሚገኙ እና እያደጉ ባሉ ሀገራትም በማዳበሪያ፣ በምግብ እና እንደነዳጅ ባሉ የኃይል እጥረት እየተጎዱ መሆናቸውን ሚስተር ማልፓስ ተናግረዋል።

በሙሉጌታ በላይ
2022-05-26