በዚህ ዓለም ሲኖሩ ተወልዶ ማደግ፣ ተምሮ መጎልመስ፣ አግብቶ ቤተሰብ መምራት የተቸሩት ፀጋዎች ናቸው።
ታዲያ ወደ ትዳር በሚደረገው ጉዞ ውስጥ ከወደፊቶ የህይወት አጋር ጋር የመተዋወቂያ ግዜ ማሳለፍ የሚጠበቅ ነው።
በመተዋወቂያ ግዜያቸው ውስጥ ፍቅረኛሞች የሚገናኙበት፣የአብሮነት ግዜን የሚያሳልፉበት ሁኔታ እና ሰዓት ለሁለቱም ወሳኝ ነው።
እርሶ ከፍቅር አጋሮ ጋር የት ቦታ በየትኛው ሰዓት ይገናኛሉ። እኛ የፍቅር አጋሩን ለማግኘት የሚኖርበትን መንደር በጨለማ ስለሚያስውጠው የመብራት ሰራተኛ ሰምተናል።
ነገሩ የሆነው በህንድ ምስራቃዊ ቢሃር ፑርኒያ አውራጃ ውስጥ በጋነሽፑር መንደር ነው። ግለሰቡ በመንደሯ የሚኖር የመብራት ሰራተኛ ነው።
ታዲያ ይህ ግለሰብ በተደጋጋሚ ከፍቅሩ ጋር በተገናኘባቸው አጋጣሚዎች ሁሉ የመንደሩ መብራት ድርግም ይላል። የመንደሯ ነዋሪዎች በምሽት ለ3 እና 4 ሰዓታት በተደጋጋሚ ቀናት በጨለማ መዋጣቸው ሀሳብ ውስጥ ይከታቸዋል። ከምንም በላይ ደግሞ ጎረቤት ያለችው መንደር በመብራት ብርሃን ደምቃ ስታመሽ የነሱ መንደር በድቅድቅ ጨለማ መዋጥ፣ ነገሩ ሆን ተብሎ የተደረገ እንደሆነ እንድያስቡ ያደርጋቸዋል።
ነዋሪዎቹ ነገሩን መመርመር ሲጀምሩ ይህ የመብራት ሰራተኛ የመንደሯን መብራት ለ3 እና 4 ሰዓታት ድርግም አድርጎ ከፍቅሩጋር አሸሸ ገዳሜ እያለ እንደሆነ ይደርሱበታል። የመንደሯ ነዋሪዎች ታዲያ እንዲሁ አንተነህ ሊሉት አልፈለጉም፤ እጅ ከፍንጅ ሊይዙት ወደዱ።
በአንደኛው ቀን የመብራት ሰራተኛው እንደለመደው መንደሯን በድቅድቅ ጨለማ ውጦ ፍቅሩን ለማግኘት ወደ ተለመደው መገናኛቸው ያቀናል። የመንደሩ ሰዎችም ተከትለውት ወደ መንደሯ ትምህርት ቤት ቅጥር ግቢ ከተፍ ይላሉ።
በግቢው ውስጥ ጥንዶቹ እንደ ጨቅላ ሕፃን ቡረቃቸውን ተያይዘውት ያገኟቸዋል።
ለአካባቢው ሰውም ይኸው በጨለማ የሚውጠንን የመብራት ቀበኛ አገኘነው ሲሉ መንደሩን አዙረው ያሳዩታል። እስከ ዛሬ በጨለማ ለዋጥከን ክፍያክ ነው ሲሉም ዱላ ቢጤ አቅምሰውታል ነው የተባለው።
መለኞቹ የመንደሩ ሰዎች እኛንም በጨለማ ከምትውጠን፤ አንተም ከምትሳቀቅ ከፍቅር አጋርህ ጋር በአንድ ጎጆ ኑር ብለው አጋብተውታል። አሁን የመንደሯ ሰዎች የወጣቶቹ መጋባት ከመብራት መጥፋት እኛም በጨለማ ከመዋጥ ተርፈናል ብለዋል።
በሳምሶን ገድሉ
2022-05-26
