ሀገሬ ቲቪ

ያልተጠቀምንበት እውቀት

ሃገራችን በሃገር በቀል እውቀቶች የታደለች ብትሆንም በተገቢው አልተጠቀምንባቸውም ተባለ። የሃገር በቀል እውቀቶቻችን ሊሰነዱ ይገባል ተብሏል።

ይህ የተባለው የባህል እና ስፖርት ሚኒስተር እና ከአምቦ ዩኒቨርሲቲ የሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድኃን የባህል ጥናት እና የምርምር ማእከል ጋር በትብብር ባካሄደው አመታዊ የባህል ጥናት እና የሃገር በቀል እውቀቶች ኮንፈረንስ ላይ ነው።

አመታዊ ኮንፈረንሱ የተካሄደው ሰላምን ለማስፈን የልሂቃን፣የሚዲያ እና የሃገር በቀል እውቀቶች ሚና በሚል መሪ ቃል ነው። በኮንፈረንሱ ላይ የተገኙት በባህል እና ስፖርት ሚኒስተር የባህል እና ቋንቋ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ የሆኑት ወ/ሮ ወርቅነሽ ብሩ ሃገራችን ኢትዮጵያ የብዙ ብሄረሰቦች መኖሪያ መሆኗ ብዙ የቀደሙ እውቀቶች እንዲኖሯት ቢያደርግም እነዚህን ሃብቶች ለትውልድ ለማስተላለፍ እና ጥቅም ላይ ለማዋል በተገቢው አልተሰራም ብለዋል።

የቀደሙ ኢትዮጵያውያን በራሳቸው እውቀት በመጠቀም መኖራቸውን የገለጹት ወይዘሮ ወርቅነሽ ከሃገር በቀል እውቀት ተጠቃሚ ለመሆን ሃብቱ እንዲመዘገብ መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።

ሃገር በቀል እውቀቶቻችንን ለሃገራዊ ሰላም እና ፋይዳ ለማዋል የሁሉም ርብርብ ያስፈልጋል ብለዋል። ለሃገር በቀል እውቀቶቻችን ተገቢ ቦታ አልሰጠናቸውም የሚሉት አባ ገዳ ተፈራ ኡጋሳ ደግሞ የምእራባውያኑ እሳቤ የበላይ ተደርጎ መታሰቡ የሃገር በቀል እውቀቶቻችንን ተጭኗቸዋል ሲሉ ለሃገሬ ቴ.ቪ ገልጸዋል።

ያልሞከርነው ርዕዮተ ዓለም የለም የሚሉት አባ ገዳ ተፈራ የግጭታችን ሁሉ ምንጭ የሃሳብ ግጭት ነው አሁን ደግሞ የሃገር በቀል እውቀቶችን እንጠቀምባቸው ብለዋል። አባ ገዳ ተፈራ በሃገር ደረጃ ሃገር በቀል እውቀቶቻችን ላይ ተነጋግረን እንጠቀምባቸው ሲሉ አሳስበዋል።

የሃገር በቀል እውቀቶቻችን በተለያዩ ምክንያቶች ተሸርሽረዋል ያሉት አባ ገዳ ተፈራ መንቃት አለብን ብለዋል። ወይዘሮ ወርቅነሽ ብሩ ሃገር በቀል እውቀቶቹ እንዲመዘገቡ ዩኒቨርሲቲዎች ጥናት እንዲያደርጉ እየተደረገ ነው ያሉን ሲሆን በባህል እና ስፖርት ሚኒስተር የባህል እና ቋንቋ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ የሆኑት የሃገር በቀል እውቀቶችን ለመሰነድ የባህል እና ስፖርት ሚኒስተር እየሰራ ቢሆንም ሁሉም እውቀቶች በተገቢው ተሰንደዋል ብለን አናምንም ብለዋል። ሁሉም ዜጋ እነዚህን እውቀቶች የመጠበቅ እና የማስተላለፍ ሃላፊነት እንዳለበትም ጠቁመዋል።

በአብርሃም በለጠ
2022-05-26