ሀገሬ ቲቪ

<<የደመወዝና የጡረታ ክፍያ ማሻሻያ >>

የሩሲያ ዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ ጊዜ ጀምሮ አሜሪካ በሩሲያ ላይ በርካታ ኢኮኖሚያዊ ማዕቀቦችን በመጣል የሩሲያን ኢኮኖሚን ለማድቀቅ ና በሀገሪቷ ያለውን የገንዘብ ዝውውር በማዳከም ከገንዘብ ተቋማት ጋር ያላትን ግንኙነት ለማስተጓጎል እየሰራች ነው በሚል በተደጋጋሚ አሜሪካ ትወቀሳለች።

አሁን ደግሞ የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ይህንን ተጽእኖ ለመቀልበስ ይመስላል በሩሲያ ዝቅተኛውን የደመወዝ እና የጡረታ ክፍያ በ10 በመቶ እያሻሻልን ነው ብለዋል።

ውሳኔው በሚያዝያ ወር 17 ነጥብ 8 በመቶ የደረሰውን የዋጋ ንረት ለመከላከል ያለመ ነው ተብሎለታል።

እንደ ፑቲን ከሆነ ከፍተኛ የዋጋ ግሽበቱ ከሩሲያ ዩክሬን ጦርነት ጋር ሙሉ በሙሉ የተገናኘ አይደለም። ፑቲን ሌሎች ሀገራትም ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት እያጋጠማቸው ነው የእኛ የተለየ አይደለም ሲሉ ተደምጠዋል።

ሮይተርስ የዜና ምንጭ በበኩሉ ሩሲያ እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰችው የተጣለባትን ከባድ ማዕቀብ ለማቋቋም ነው ብሏል።

በፈረንጆቹ 2022 ለሩሲያ ፈታኝና አስቸጋሪ ዓመት ነበር ሲሉ የገለጹት ፑቲን ሁሉም የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ጉዳዮች ከጦርነቱ ጋር የተገናኙ ናቸው ተብሎ በበርካቶች የሚነሳውን ሀሳብ እንደማይቀበሉ ግን ተናግረዋል።

ምክንያቱም ይላሉ ፑቲን ምንም አይነት የጦርነት እንቅስቃሴ በማይደረግባቸው ሀገራት በሰሜን አሜሪካና በአውሮፓ የዋጋ ግሽበቱ ከኛ ጋር ሲነጻጸር ያየለ ነው ብለዋል።

የሩስያ የዋጋ ግሽበት በሚያዝያ ወር 17.8 በመቶ ነበር፤ የአሜሪካ የዋጋ ግሽበት ደግሞ 8.3 በመቶ ነው ሲል ሮይተርስ የፑቲንን መግለጫ ተቀርኖ ጽፏል።

የሩሲያው መንግሥት ዝቅተኛው የደመወዝ እና የጡረታ ጭማሪ በፈረንጆቹ ሰኔ 1 ተግባራዊ ለማድረግ አቅዷል። አሁን ያለው ዝቅተኛ ደመወዝ በወር 13 ሺሕ 890 ሩብል ወይም ሁለት መቶ ሠላሳ ሦስት ዶላር ሲሆን አማካኝ የጡረታ አበል በወር 18 ሺሕ 521 ሩብልስ ወይም 311 ዶላር ነው ።

በየካቲት ወር ጦርነቱ ከተጀመረ በኋላ በሩሲያ ከፍተኛ ማዕቀብ መጣሉ ይታወሳል። ከዓለም ዓቀፍ የፋይናንስ ኢንስቲትዩት የተውጣጡ የንግድ ባለሙያዎች አደረግን ባሉት ጥናት የሩሲያ ኢኮኖሚ “እየተሽመደመደ" ነው።

በፈረንጆቹ በ2022 መገባደጃ ላይም የሩሲያ ጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት (ጂዲፒ) በ30 በመቶ ይወድቃል ብለው ገምተዋል። ፑቲን በበኩላቸው የሩሲያ ኢኮኖሚ በአንዳንድ ባለሙያዎች እንደተገመተው አይደለም በማለት በአቋማቸው ጽንተዋል ሲል ፋይናንሺያል ታይምስ ዘግቧል።

ፑቲን በ2022 የዋጋ ግሽበቱ ከ15 በመቶ በላይ ይሆናል ብለው እንደማይጠብቁ ኤፍቲ ዘግቧል። የሩሲያ ማዕከላዊ ባንክ ደግሞ በዚህ ዓመት ከ 18 እስከ 23 በመቶ የዋጋ ግሽበት እንደሚኖር ተንበያውን አስቀምጧል።

በመቅደስ እንዳለ
2022-05-27