በሰሜን ኢትዮጵያ በተደረገው ውጊያ ሰለባ ከሆኑ መካከል የዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር አንዱ ነው በዚህ አስተዳደር ስር የሚገኙ ዜጎች ከጦርነት ሽሽት ከቤት ንብረታቸው ከተፈናቀሉ ጊዜያት ነጉደዋል፡፡በዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር የአደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ ሰለሞን ንጉስ ከሀገሬ ቴሌቭዥን ጋር ባደረጉት የስልክ ቆይታ ከሳምንት በፊት በተደረገ ጥናት 80 ሺሕ 397 ተፈናቃዮች መኖራቸውን ነግረውናል ፡፡ ይህ ቁጥር 90 ሺሕ ሊደርስ እንደሚችል ተገልጿል፡፡
“ከዚህ ውስጥ ከ7 ሺሕ 165 አዲስ አጥቢ እናቶች ሲሆኑ ከ2 ሺሕ 821 በላይ የሚሆኑ ነፍሰጡሮችም በሰቆቃ ላይ ናቸው፡፡ በዚህ ሁኔታ ከቀጠለ እጅግ አስጊ ነው፡፡”
ከተፈናቃዮች ውስጥ አብዛኞቹ ሴቶች፣ህጻናት፣አረጋውያን ፣ወላጅ አልባ ህጻናት እና አካል ጉዳተኞች፣ነብሰጡሮች በመሆናቸው ከፍተኛ ድጋፍን ይሻሉ፡፡
“18 ሺሕ ገደማተፈናቃዮች ብቻ ናቸው በመጠለያ ያሉት ከ70 ሺሕ በላይ ተፈናቃዮች ከመጠለያ ውጪ ናቸው፡፡ በዚህ ሁኔታ የሚቀጥል ከሆነ እዚሁ የሚወለዱ ህጻናት ይኖራሉ ይላሉ፡፡” ብለዋል ኃላፊው፡፡
የክልሉመንግሥትን ጨምሮ ዓለም አቀፍ ግብረሰናይ ድርጅቶች ፣በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ አቡነ በርናባስ፣የዋግ ልማት ማህበር፣የአማራ መልሶ ማቋቋም እና ሌሎችም ድጋፍ ያደረጉ ቢሆን አሁንም በርካታ ዜጎች እየተራቡ ስለመሆኑ እና ከፍተኛ ችግር ውስጥ ስለመሆናቸው ነግረውናል፡፡
የምግብ እጥረቱ ከፍተኛ በመሆኑ ለህጻናት አልሚ ምግቦች የንጽህና መጠበቂያ እቃዎች፣አንሶላና ብርድልብሶች እና ሌሎችም ድጋፎች ያስፈልጋል ተብሏል፡፡
የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ መጪው ጊዜ ክረምት እንደመሆኑ መጠለያን ጨምሮ ከፍተኛ የምግብ እጥረት ፣የታማሚዎች ቁጥር መጨመር እና መሰል ችግሮች በዜጎች ላይ እየደረሰ መሆኑን በመመልክት ዜጎች ለዋግ ሕዝቦች እጃቸውን እንዲዘረጉ ጠይቀዋል፡፡
በፍሬህይወት ታደሰ
2022-05-27
