ሀገሬ ቲቪ

በሰዎች ችሎት የተፈረደበት በግ

ሰዎች ሲያጠፉ ይዳኙበት ዘንድ ዳኛ ተሰይሞላቸው ነገረፈጅ ተመርጦላቸው ችሎት ይቆማሉ።

ሰልጥነናል በሚሉት ዓለም ውስጥ ሰው ላይ ግፍ የዋለን ብቻም ሳይሆን ጠባቂ እና ተከራካሪ የላቸውም የሚባሉትን እንስሳት ዝንባቸውን እሽ ያለ ሲፈረድበት ሰምተናል።

እንዲህ አይነቱ የፍርድ ሂደት ታዲያ ሰዎችን እንጂ እንስሳትን ሲዳኝ ታይቶም ተሰምቶም አይታወቅም። እኛ አንድ በግ በነፍስ ማጥፋት ወንጀል ተከሶ ፍርድ ቤት ቀርቦ እንደነበር ሰማን እና ልናጋራችሁ ወደድን።

ነገሩ ጎረቤት ሀገር ሱዳን ውስጥ የሆነ ነው። በሱዳን ሩምቤክ የሚገኝ አንድ በግ አንዲት አዛውንትን በግንባሩ ገጭቶ የጎድን አጥንቶቿ ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል ይለናል የሱዳን የዜና ወኪሎች ዘገባ።

በርግጥ በጣም የዋህ ከሚባሉት እንስሳት መካከል የሚመደብ ነው በግ። በየዋህነታቸው የምናውቃቸውን ሰዎች ሳይቀር የዚህን እንስሳ ስም እናጎናፅፋቸዋለን።

ይኸው በግ ታዲያ አሁን ተከሶ፤ ፍርድ ቤት ቀርቦ፤ ተፈርዶበታል። በበጉ ግንባር የተነረቱት አዛውንት ወዲያውኑ ህይወታቸው አልፏል። በዚህም ሳቢያ ፖሊስ አስፈላጊውን ምርመራ አድርጌ ይፈረድበት ዘንድ ፍርድ ቤት በጉን አቅርቤዋለው ብሏል።

በጉም በቀረበበት ክስ ጥፋተኛ ተብሎ ለሦስት ዓመታት በእስር እንዲያሳልፍ ተፈርዶበታል። ፍርድ ቤቱ ለገዳይ ባለቤትም ቅጣትን ጥሏል። አምስት ላሞችን ካሳ ይክፈል ሲል።

ጥቃት አድራሹ በግ ታዲያ ሦስት ዓመታትን በወታደራዊ ካምፕ በእስር ካሳለፈ በኋላ የሟች ቤተሰቦች ያሻቸውን እንዲያደርጉት ተላልፎ ይሰጣል ነው የተባለው።

የአካባቢው የፖሊስ አዛዥ እንዳሉት ከሆነ ወንጀሉን የፈፀመው በጉ ነው ስለዚህ ባለቤቱ ሊታሰር አይገባም፤ በጉ ግን ለፈፀመው ጥቃት እስር ይገባዋል ብለዋል።

በዚህ ሁሉ መሀል በጉ ጠበቃ ቆሞለት ለመብቱ ይሟገትለት አይሟገትለት ዘገባው ያለው ነገር የለም። የተጎጂ እና የጎጂ ቤተሰቦች ግን በፍርዱ መስማማታቸውን በፊርማቸው አፅድቀዋል። ፖሊስ እና የአካባቢው ማህበረሰብ መሪዎችም ለፍርዱ ምስክር ነን ሲሉ ተገኝተውም ነበር።

በሳምሶን ገድሉ
2022-05-27