በኢትዮጵያ የሆቴል እና ቱሪዝም ዘርፉ የተለያዩ ለውጦችን እያስተናገደ ዛሬ የደረሰበት ደረጃ ላይ ቢደርስም አሁንም የተለያዩ ችግሮችን እያስተናገደ ይገኛል፡፡
በተለይ ዘርፉን ለማሻሻል እና ዓለም ከደረሰበት ደረጃ ላይ ለማድረስ የሚረዱ ጥናቶች አለመኖራቸው ለኢንዱስትሪው አለማደግ ከፍተኛ አስተዋፆ አላቸው ሲሉ የኢትዮጵያ ቱሪዝም ሆቴል ማርኬቲንግ ፕሮፌሽናል አሶሴሽን ፕሬዝዳንት ጌታሁን ዓለሙ ተናግረዋል፡፡
የሆቴል ቱሪዝሙ አንዱ ክንፍ በሆነው የምግብ እና መጠጥ አገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያም የተሰሩ ስራዎች አለመኖራቸው እና ባህላዊውን ከዘመናዊ አሰራር ጋር ማካተት አለመቻሉ ትልቅ ችግር መሆኑን ተነስቷል፡፡
እነዚህን ችግሮች አጉልቶ ለማሳየት እና የመፍትሄ ሀሳቦችን ለማመንጨት የምግብ እና መጠጥ አገልግሎት አሰጣጡ ትላንት የት ነበር ዛሬስ ምን ላይ ነው በሚል ዳማት የሆቴልና ቢዝነስ ኮሌጅ ያዘጋጀው የምክክር መድረክ በአዲስ አበባ ባሳለፍነው ሳምንት ተዘጋጅቷል፡፡
በምክክር መድረኩ ላይ ፅሁፍ ያቀረቡት እና የሆቴል ቱሪዝም አማካሪ የሆኑት አቶ መልካሙ መኮንን በሆቴል የምግብ እና መጠጥ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የተለያዩ ተግዳሮቶች መኖራቸውን አንስተዋል፡፡
በመድረኩ ላይ ተሳታፊ የሆኑት የሆቴል እና ቱሪዝም ባለሙያዎችም የሆቴል ቱሪዝሙ ያላደገው በውስጡ የሚሰሩ ሰራተኞች በራሳቸው የሚሰጡትን አገልግሎት ባለማወቃቸው ነው ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ባህላዊ ምግቦች እና መጠጦች በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እየሆኑ ቢመጡም በመስተንግዶ እና ድጋፍ አሠጣጥ ላይ ዘመናዊ እና በሙያው በሰለጠኑ ባለሙያዎች ሙሉ ለሙሉ አለመያዙ አሁንም ወደ ፊት እንዳይሄድ አድርጎታል ተብሏል።
በዳማት ሆቴል እና ቢዝነስ ኮሌጅ ሀሳብ አመንጪነት በተዘጋጀው ይኸው ሴሚናር ላይ የተገኙት የሆቴል እና ቱሪዝም አማካሪው አቶ ፍሰሀ አስረስ ዘርፉ ላይ እየታየ ያለውን ለውጥ አጠናክሮ ለማስቀጠል የሰው ሀይል ላይ መሰራት አለበት ብለዋል፡፡
“አሁን ያለውን ሁኔታም ለማሻሻል በደንበኞች ፍላጎት ላይ ያተኮረ አገልግሎት መስጠት አዋጭ ይሆናል፡፡” ሲሉ አክለዋል፡፡እንደ አቶ ፍሰሃ ገለጻ “የሆቴል ቱሪዝሙ ላይ የተሳተፉ ኢንቨስተሮችም የመጀመሪያው ተጠያቂዎች በመሆናቸው ዘርፉ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ በጋራ መስራት ይጠበቅባቸዋል፡፡”
መንግሥትም ባለድርሻ እንደመሆኑ መጠን በሆቴል ዘርፉ ላይ በተለይ በምግብ እና መጠጥ አገልግሎት አሠጣጥ ላይ የተለያዩ ፖሊሲዎችን በማውጣ ዘርፉን ሊደግፍ ይገባል የሚል ሃሳብም ቀርቧል፡፡
እንደ ዳማት ሆቴል እና ቢዝነስ ኮሌጅ በዘርፉ ላይ የሚያሰሯቸው ጥናቶች በዘርፉ ላይ ለውጦች እንዲመጡ ብቻ ሳይሆን መንግሥት ዘርፉን ተኮር የሆነ ፖሊሲ እንዲቀርፅ እና በቀረፃው ወቅትም ጭምር ግብዓት ይሆናሉ ተብሏል፡፡
በፍሬህይወት ታደሰ
2022-05-31
