ሀገሬ ቲቪ

የአውሮፓ ኀብረት የመጨረሻ ውሳኔ

ሩሲያ ለጦር መሣሪያዋ ትልቅ የፋይናንስ ምንጯ ነው በሚል የምትትታመበት የነዳጅ ዘይቷ በአውሮፓ ኀብረት ሊታገድ መሆኑ ተሰምቷል።

የአውሮፓ ህብረት ሹሞች ከሃንጋሪ ጋር ስምምነት ካደረጉ በኋላ ነው የሩሲያ የነዳጅ ዘይትን ለማገድ ውጥን መያዛቸው የተሰማው ።

ህብረቱ በያዝነው የፈረንጆቹ ዓመት ማገባደጃ ከሩሲያ ወደ 90 በመቶው የሚገቡትን የነዳጅ ምርቶች ለመቀነስ ታልሟል። እገዳው ሩሲያ ዩክሬንን ለመውረር የምትጠቀመውን የገንዘብ ምንጭ ለማድረቅ ስምምነቱ ያግዛል ተብሎለታል።

በብራስልስ በተካሔደው ስብሰባ ሹማምንቱ የዓለማችን ረጅሙ የዘይት ቧንቧ መስመር እንዲሁም በዓለም ላይ ካሉ ትልቁ የነዳጅ መስመር ኔትወርኮች አንዱ በሆነው በድሩዝባ የቧንቧ መስመር ወደ አውሮፓ የሚደርሱ ምርቶችን ነፃ ለማድረግ ስምምነትን አስረዋል።

የአውሮፓ ምክር ቤት ኅላፊ ቻርለስ ሚሼል በትዊተር የማኅበራዊ ትስስር ገፃቸው እገዳውን አስመልክተው “ጦርነቱ እንዲቆም በሩሲያ ላይ ከፍተኛው ጫና” ሲሉ ጽፈዋል።

ወደ አውሮፓ ህብረት ከሚገባው የሩስያ ዘይት ውስጥ ሁለት ሶስተኛው በታንከር እና አንድ ሶስተኛው በድሩዝባ የቧንቧ መስመር ይደርሳል።

ከቧንቧው ጋር የተገናኙት ፖላንድ እና ጀርመን የሩሲያን ዘይት በዓመቱ መጨረሻ መውሰድ ካቆሙ በኋላ ማዕቀቡ 90 በመቶ ይደርሳል።

ቀሪው 10 በመቶው ሃንጋሪ፣ ስሎቫኪያ እና ቼክ ሪፐብሊክ ከደቡባዊው የቧንቧ መስመር ጋር የተገናኙት በቀላሉ መተካት የማይችሉትን ነዳጅ ማግኘት እንዲችሉ ለጊዜው ከማዕቀብ ነፃ ይሆናል።

በስምምነቱ የሩሲያ ትልቁን ባንክ ሰበር ባንክ ን ከዓለም ዓቀፉ የስዊፍት ሲስተም ማቋረጥንና በጦር ወንጀሎች የተከሰሱ ግለሰቦችን ተጠያቂ ማድረግን ጨምሮ ሌሎች እርምጃዎችም ተግባራዊ ሊሆኑ ይችላሉ ሲል አልጀዚራ ጽፏል።

የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ ከጉባኤው ቀደም ብለው ባደረጉት የተንቀሳቃሽ ምስል ንግግር የአውሮፓ ህብረት መሪዎች በሞስኮ ላይ የሚያሳዩትን ለስላሳነትን ነቅፏል።

“ለምንድነው ሩሲያ ሃይል በመሸጥ በቀን አንድ ቢሊዮን ዩሮ የሚጠጋ ገንዘብ የምታጋብሰው?” ዘለንስኪ ጠይቋል። በአሜሪካ በሚገኘው የሂዩስተን ዩኒቨርሲቲ የፔትሮሊየም ምህንድስና ፕሮፌሰር የሆኑት ራማናን ክሪሽናሞርቲ ስምምነቱ በሩስያ ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ የታሰበውን ያህል ላይሆን ይችላል ሲሉ ስጋታቸውን ተናግረዋል።

እገዳው ለኢራን እና ለቬንዙዌላ ይልቅ አዎንታዊ ተጽእኖ ሊኖረው እንደሚችል ፕሮፌሰሩ ጠቁመዋል። ከአውሮፓ እና ከአሜሪካ ጋር ስምምነት ፈጥረው ምርታቸውን ወደ ዓለም ገበያ የማስገባት አቅማቸውን ሊያሰፉ ይችላሉ ብለው ተንብየዋል ፕሮፌሰሩ።

መሪዎቹ ከጦርነቱ በኋላ ዩክሬንን መልሶ ለመገንባት ዓለም አቀፍ ድጋፍ መፈጥረን ቀጣይ እንደሚያተኩሩበት በመረጃው ተጠቅሷል፡፡

በመቅደስ እንዳለ
2022-05-31