ሀገሬ ቲቪ

ኬክ የተወረወረባት ሞናሊዛ

በዓለማችን ላይ ካሉ በርካታ የሰው ልጅ የእጅ ስራዎች በብዛት የተጎበኘች፣ በአያሌው የተዘፈነላት፣ እጅግ የበረከቱ ጽሑፎች የተፃፈላት ናት ሞናሊዛ።

እውቁ የጣልያን የጥበብ ሰው ሊዮናርዶ ዳቬንቺ ይህቺን ስዕል እንደ ምዕራባእያኑ የዘመን ቀመር በ1503 እንደሳላት ይታመናል። ሰዓሊው የሳላት ሴትም የመኳንንቱ ቤተሰብ የፍራንቼስኮ ዴል ጆኮንዶ ሚስት እንደነበረች በርካታ ዘርፉን ያጠኑ ሰዎች ያምናሉ።

ስዕሉ ከጣሊያን የሕዳሴ ዘመን የጥበብ ውጤቶች ውስጥ ከሚጠቀሱት ቀዳሚው ነው።

ይህንን ማንሳታችን ያለምክንያት አይደለም አንድ ዊግ የለበሰ ሰው በሞናሊዛ ስዕል ላይ ኬክ በመወርወሩ ለእስር ተዳርጓል መባሉን ብንሰማ ነው።

ግለሰቡ በፓሪስ በሚገኘው ሉቭር ሙዚየው ውስጥ በክብር፣ በመስታወት መጠበቂያ ውስጥ ባለችዋ ሞናሊዛ ላይ ኬክ ወርውሯል።

ባለዊጉ ሰው ቀይ አበባን በእጁ እንደያዘ ወደ ሞናሊዛ መጠበቂያ መስታዎት ከተጠጋ በኋላ በእጁ የያዘውን ኬክ ወደመስታወቱ ወርውሮታል።

በስፍራው የነበሩት የሚዚየሙ ጠባቂዎች ግለሰቡን አንከውክወው ለፖሊሶች አሳልፈው ሰጥተውታል። ይህ የ36 ዓመት ሰው በፖሊሶች ከመወሰዱ አስቀድሞ በጩኸት ሰእዎች ለአልባሌ ነገር ሳይሆን ለፕላኔቷ እንዲጨነቁ አሳስቧል።

“ምድርን አስቡ! ምድርን የሚያጠፉ ሰዎች አሉ! አስብበት። አርቲስቶች ይነግሯችኋል። ስለ ምድር አስቡ። ይህን ያደረግኩት ለዚህ ነው" ሲል።

ይህ የግለሰቡ ድርጊት በማሕበራዊ ፅር ገፆች ላይ ከተለጠፈ በኋላ በርካቶችን አነጋግሯል። የፓሪስ አቃቤ ህግ መቼም ጤነኛ ሰው መልካም መልዕክትን ለማስተላለፍ ጥፋትን አይጠቀምም ሲል በፖሊስ የተያዘውን ባለዊግ ወደ አዕምሮ ህክምና ማዕከል እንዲገባ አድርጎታል። በግለሰቡ ላይም ምርመራ ተጀምሯል ነው የተባለው።

የህዳሴ ዘመን የሚባለው የ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ድንቅ ስራ የሆነው ስዕሉ ከ500 ዓመታት በላይ አስቆጥራል። ስዕሉ እንደ ምዕራባውያኑ በ1911 በሙዚየም ሰራተኛ ተሰቆ ነበር። በግዜው ድርጊቱ የስዕሉን ዓለም አቀፍ ዝና ከፍ አድርጓል።

እንዲሁም በ1950ዎቹ በአንድ ግለሰብ በደረሰበት የአሲድ ጥቃት ተጎድቶም ነበር። ከዚያን ግዜም ጀምሮ ስዕሉ በመስታዎት መጠበቂያ ውስጥ ከሰዎች ንክኪ እንዲርቅ ተደርጓል።

የዚህ ስዕል መከራ እንዲህ የሚያበቃም አልነበረም በ2009 አንዲት ፈረንሳይ ፓስፖርት አልሰጠችኝም በሚል የሸክላ መጠጫዋን በዚህ ስዕል ላይ ወርውራም ነበር። የስዕሉን መጠበቂያ መስታወት ብቻ ብታገኝም።

ታዲያ ይህ ሞና ሊዛ የተሰኘ ስዕል በዓለም ላይ ካሉት በጣም ውድ ሥዕሎች አንዱ ነው። እንደ ምዕራባውያኑ በ1962 በ100 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር (በ2021 ከ870 ሚሊየን ዶላር ጋር እኩል) ለዚህ ስዕል የተገባ ውዱ የመድን ገንዘብ ተደርጎ በዓለም ድንቃድንቅ መዝገብ ላይ ሊካተት ችላል።

በሳምሶን ገድሉ
2022-05-31