የትምህርትና ስልጠና ባለስልጣን ተቋማዊ እውቅናና እድሳት ሳያገኙ ማስተማር፣ ያልተፈቀደላቸውን የትምህርት መስክ ማስተማር፣ እውቅና የሌላቸውን ቅርንጫፍ ኮሌጆች መክፈት የመሳሰሉ ህገ-ወጥ ተግባራትን የሚፈጽሙ ተቋማት እየተበራከቱ ነው ብሏል።
የትምህርትና ስልጠና ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አንዱ ዓለም አድማሴ ባለፉት አስር ወራት የህግ ጥሰት በፈጸሙ 144 የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ላይ እርምጃ ሲወሰድ 60 ተቋማት ላይ ደግሞ እስከመዝጋት የሚደረስ እርምጃ ተወስዷል ብለውናል።
ባለስልጣኑ በቀጣይም ተቋማቱን ከመዝጋት ባለፈ በከፍተኛ ትምህርት ተቋም ውስጥ አካዳሚክ ጉዳዮች ላይ ውሳኔ ሰጭ አካል የሆነው ሴኔት በፈርመው ፊርማ በፍትኃብሄርና በወንጀል ልጠይቅ መሰናዳቴን እወቁልኝ ብሏል።
ህብረተሰቡ በህገወጥ ተቋማት ተመዝግቦ ጊዜውንና ገንዘቡን ከማባከን እንዲቆጠብና በተቋሙ የማሕበራዊ ትስስር ገጾች በመግባት መረጃዎችን እንዲከታተል በባለስልጣኑ ተመክሯል።
እርምጃ ከተወሰደባቸው ተቋማትም መካከል ምንም ዓይነት እውቅና የሌላቸው መኖራቸውን ከተቋሙ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
በመቅደስ እንዳለ
2022-06-01
