በዚህ ዓለም የሚኖር ሁሉ ይወለዳል ያድጋል ያረጃል ይሞታል።
ይህ የተፈጥሮ ህግ ነው። ይህ የተፈጥሮ ህግ ታዲያ ለሰው ልጆችም ብቻም ሳይሆን ለእፅዋትም ይሰራል።
ይህንን የተፈጥሮ ህግ የሻረ በሺሕዎች የሚቆጠሩ ዘመናትን ህያው ሆኖ መኖር የቻለ ዛፍ ተገኘ መባሉን ሰማን።
በቺሊ የሚገኙ ተመራማሪዎች ናቸው አዛውንቱን ዛፍ እድሜውን አውቀናል ያሉት።
ተመራማሪዎቹ፤ ታላቅ አያት በሀገሬው አጠራር ደግሞ ግራን አቡሎ ተብሎ የሚጠራው አዛውንት ዛፍ 5ሺሕ 484 ዓመታትን በህይወት መሻገር ብቻም ሳይሆን ዛሬም በህይወት ያለ ዛፍ ነው ብለዋል።
ፓታጎኒያ ሳይፕረሶች በሺሕዎች የሚቆጠሩ ዓመታትን የመሻገር አቅም እንዳላቸው ይታመናል።
በቁመታቸውም እስከ 45 ሜትር ድረስ መመዘዝ ይችላሉ።
የእነዚህ ዝርያ የሆነው ዛፉ 5 ሺህ ዓመታትን በመሻገር የሚወዳደረውም የለም ነው የተባለው።
አዛውንቱ ዛፍ በአሌርሴ ኮስቴሮ ብሔራዊ ፓርክ ውስጥ በመቾት እየኖረ ይገኛል።
የቺሊ የተመራማሪዎች ቡድን ግኝት የሚረጋገጥ ከሆነ ዛፉን አንጋፋ ጥንታዊ ዛፍ ያደርገዋል።
ዛፉ ከዚህ ቀደም አዛውንት ተብላ በካሊፎርኒያ የምትገኘውን የ4,853 ዓመቷን የብሪስትሌኮን ጥድ የአዛውንትነት ማዕረግ ይነጥቃል።
እንደ አለመታደል ሆኖ ይላሉ የዘርፉ ተመራማሪዎች የዓለም ሙቀት መጨመር እና ሰዎች የፓታጎኒያን ሳይፕረስ ዝርያ ዛፎችን ማጥፋት የዚህን ጥንታዊ ፍጡር ሕልውና አደጋ ላይ እየጣለ ነው።
እስካሁን ድረስ ባዓለማችን ላይ በሕይወት ለመኖር እድል ያገኙት የዚህ ዛፍ ዝርያዎች 28 በመቶው ብቻ ናቸው።
የተቀሩት በአየር ንብረት ለውጥ እና በሰዎች ምክንያት ትላንት ሆነው ቀርተዋል።
በሳምሶን ገድሉ
2022-06-01
