ዛሬ እለቱን ከታሪክ አይነ ስውር እና መስማት የተሳናት ብትሆንም በአለም እውቅ መሆን ስለቻለችው ጸሃፊ እና መምህርት ሄለን ኬለር እንነግራችኋለን። ከተወለደች ከ19 ወራት በኋላ ጀምሮ መስማትም ማየትም ያልቻለችው ሄለን ኬለር ከሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ የክብር ዲግሪ በማግኘት የመጀመሪያዋ ሴት መሆን ችላለች። ለማየት እና መስማት አለመቻል ያለውን መድሎ እና የግንዛቤ እጥረት ለማጥራት ሰርታለች። ሄለን ኬለር ያረፈችው በ87 አመቷ በዛሬዋ እለት ከ54 አመታት በፊት በፈረንጆቹ 1968 ነበር።
ሄለን አዳምስ ኬለር የመስማት እና የማየት እክል ቢኖርባትም አለም ላይ እውቅ ከመሆን አላገዳትም። ሄለን ኬለር የተወለደችው በአሜሪካ በአላባማ ቱስኩምባ አካባቢ ባለ የእርሻ ቦታ በፈረንጆቹ 1880 ነው። ስትወለድ ጤናማ የነበረችው ሄለን ኬለር በተወለደች በ19 ወሯ በመታመሟ አይነ ስውር እና መስማት የተሳናት መሆኗ የግድ ሆነ።
ለቀጣዮቹ አራት አመታት ዝምተኛ እና አመጸኛ ህጻን ሆና በቤት ቆየች። ለአይነ ስውር እና መስማት ለተሳናቸው የሚሰጥ የልዩ ፍላጎት ትምህርት በጊዜው ገና መጀመሩ ነበር። ቤተሰቦቿ አይኗ በአይን ሃኪም እንዲመረመር ያደረጉት ከስድስት አመቷ በኋላ ነበር።
ኬለርን የስልክ ፈጠራ ባለቤት የሆነው አሌክሳንደር ግራሃምቤል ጋር እንድትገናኝ አደረጓት። አሌክሳንደር ግራሃም ቤል መስማት ለተሳናቸው የንግግር ክህሎትን በማስተማር ቀዳሚ ነው። ቤል ሄለን ኬለርን ከመረመረ በኋላ በቦስተን ከሚገኘው ከፐርኪንስ ተቋም የአይነ ስውራን መምህር እንዲላክላት አደረገ።
የ20 አመቷ መምህርት አኔ ሱሊቫን ከፊል አይነ ስውር ነች። በፐርኪንስ አይነ ስውር እና መስማት የተሳናቸው ተማሪዎች የእጅ ፊደሎችን በመዳፋቸው እንዲነኩ በማድረግ መግባባት እንዲችሉ ታሰለጥናለች። ይህችው መምህርት ታዲያ ለሰባት አመቷ ሄለን ኬለር ይሄንንው የመግባቢያ መንገድ ለማስተማር ወደ ቱስኩምባ ተጓዘች።
ሱልሊቫን ኬለርን ማስተማር ጀመረች። ሄለን ኬለር ስለጽሁፍ ቋንቋ እውቀቱ አልነበራትም። ግና ደግሞ ‘Water’ ውሃ የሚለውን የመጀመሪያ ቃሏን በቀናት ውስጥ ተማረች። ኋላ ኬለር ሁነቱን “ውሃ ማለት አስገራሚው በእጄ ላይ የሚፈሰው አስደናቂው ቀዝቃዛ ነገር እንደሆነ አወቅሁ። ያ ህያው ቃል ነፍሴን አበራት፤ ብርሃን፣ ተስፋ፣ ደስታ ሰጠኝ፤ ነጻ አደረገኝ።” ነበር ስትል የገለጸችው።
የሰባት አመቷ አይነ ስውሯ እና ኬለር በሱሊቫን ስር በሚያስገርም ፍጥነት ቃላቶችን ተማረች። አረፍተ ነገር መመስረት ጀመረች። ከዚያም ሙሉ ጽሁፍን ማንበብ ቻለች። በወራት ውስጥ የሚደንቅ የመማር ፍጥነት ያሳየችው ኬለር ከአመት በኋላ ብሬይል ማንበብ የተማረችበትን ፐርኪንስ ኢንስቲትዩሽንን ጎበኘች።
ኬለር እ.ኤ.አ. በ1890 በሆራስ ማን የመስማት የተሳናቸው ትምህርት ቤት ከሳራ ፉለር የንግግር ክህሎትን ተምራለች። ኬለር ከሳራ ፉለር መናገርን የተማረችው የከንፈር እንቅስቃሴን ለመገንዘብ እጆቿን ከፉለር ከንፈሮች እና ደረት ላይ በማስቀመጥ ነው። ስትናገር ግን አስተርጓሚ ያስፈልጋት ነበር። ብዙ ጊዜም ሱሊቫን ለድምጿ ቅርበት ስለነበራት ትተረጉምላት ነበር።
የ14 አመቷ ኬለር በኒው ዮርክ ራይት ሁማሰን የተሰኘውን መስማት የተሳናቸው ትምህርት ቤትን ተቀላቀለች። ከሁለት አመታት በኋላ በማሳቹሴት የካምብሪጅ ትምህርት ቤትን ከኬለር ጎን ሱሊቫን መዳፎቿ ላይ እየጻፈችላት የወጣት ሴቶች ትምህርት ቤትን ተቀላቀለች።
እ.ኤ.አ. በ 1900 በካምብሪጅ ውስጥ በሚገኘው የሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ መምህራን በሚያስተምሩበት ታዋቂ የሴቶች ኮሌጅ ራድክሊፍን ተቀላቀለች። በራድክሊፍ ጎበዝ ተማሪ የነበረችው ኬለር በዚያው ሳለች የህይወት ታሪኳ ‘The Story of My Life’ በሚል ‘The Ladies Home Journal’ ላይ በተከታታይ ለንባብ የበቃ ሲሆን ኋላም በፈረንጆቹ 1904 በመጽሃፍ መልክ ታትሟል። ከራድክሊፍም መመረቅ ችላለች።
ከራድክሊፍ ዲግሪ በማግኘት የመጀመሪያዋ አይነ ስውር እና መስማት የተሳናት መሆን የቻለችው ሄለን ኬለር ኋላም ከሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ የክብር ዲግሪ በማግኘት የመጀምሪያዋ ሴት መሆን ችላለች።
ኬለር በተለያየ ጊዜ የተለያዩ መጻህፍትን በመጻፍ የተዋጣላት ጸሃፊ መሆኗን አስመስክራለች።
‘The World I Live In ‘(1908)፣ ‘Out of the Dark ‘(1913)፣ ‘My Religion’ (1927)፣ ‘Helen Keller’s Journal ‘(1938) እናTeacher (1955) የተሰኙ መጻህፍትን ማሳተም ችላለች።
በፈረንጆቹ 1913 በተርጓሚ እገዛ ማስተማር ጀምራለች። መጀመሪያ ማስተማር የቻለችው ለአይነ ስውራን የአሜሪካ ፋውንዴሽን ነበር። የማስተማር ጉዞዎችን በአለም ዙሪያም ማድረግ ችላለች። የማየት እና የመስማት እክል ላይ ያለውን መድሎ እና የተዛባ ምልከታም ለመቀየር ብዙ ጥራለች። በህይወት ዘመኗን ሶሽያሊዝምን ትደግፍ ነበር።
አይነ ስውርም መስማት የተሳናትም ሆና ለሰራችው ስራ ከፍተኛ ክብር ማግኘት ችላለች። በፈረንጆቹ 1964 ከፕሬዚደንት ሊንደን ቢ ጆንሰን የ ሜዳል ኦፍ ፍሪደም ሽልማትን ማግኘት ችላለች።
ማየትም መስማትም አለመቻል ከከፍታው ያላገዳት ኮከብ ሄለን ኬለር።
በአብርሃም በለጠ
2022-06-01
