ሀገሬ ቲቪ

እለቱን ከታሪክ - ‘የሬድዮ አባት’ የገመድ አልባ ተግባቦት ጀማሪ

አለም ዛሬ ላይ ገመድ አልባ የተግባቦት ቴክኖሎጂዎችን ከመቼውም ጊዜ በላይ ይጠቀማል። ወደ መጀመሪያዎቹ የግኝቶቹ ባለቤቶች መለስ ስንል ጉግሊሞ ማርኮኒን በዘርፉ ቀዳሚው ሰው ሆኖ እናገኘዋለን።

ማርኮኒ ታዲያ በእንግሊዝ የሬድዮ ሞገድን በመጠቀም የገመድ አልባ ተግባቦት ግኝቱ ባለቤትነትን ያገኘው በዛሬዋ እለት በአውሮፓውያኑ የዘመን ቀመር በ1896 ነበር። በዚሁ ፈጠራውም ‘የሬድዮ አባት’ ተብሎ ይጠራል። የዛሬው እለቱን ከታሪክ ትኩረቱን ከዚህ ላይ ያደርጋል። ጣሊያናዊው ጉግሊሞ ማርኮኒ ለገመድ አልባ ተግባቦት ጅማሮ ባለውለታ ነው። ጉግሊሞ ማርኮኒ ውልደቱ በፈረንጆቹ 1874 በጣሊያን ቦሎኛ ነው። የመሬት ከበርቴ ልጅ የነበረው ማርኮኒ በዚያው በቦሎኝ ትምህርቱን ተከታትሏል።

በሊቮርኖ ቴክኒካል ኢንስቲትውት እና በቦሎኛ ዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን መከታተል ችሏል። ማርኮኒ በጀርመኑ ፊዚስት ሄነሪክ ሩደልፍ ኸርዝ የማይታዩ ሞገዶች የኤለክትሮማግኜቲክ ግንኙነት ግኝት ተስቧል። በዚህ ግኝት ግኝ ተስቦ አልቀረም፤ የራሱን የኤለክትሮ ማኜቲክ ሲግናልን መላክ የሚችሉ ቁሳኡሶችን በቤተሰቦቹ መኖሪያ ውስጥ መገንባት ችሏል።

ግና ደግሞ የጣሊያን መንግስት በማርኮኒ ስራዎች ላይ ፍላጎት አላሳደረም። የሃገሩ መንግስት ትኩረት አናሳ መሆኑን የተገነዘበው ጉግሊሞ ማርኮኒ ወደ እንግሊዝ ለንደን በመጓዝ እድሉን ለመሞከር ቆረጠ። ወደ እንግሊዝ ከእናቱ ጋር የተጓዘው የ22 አመቱ ማርኮኒ ስራው የእንግሊዝ የፖስታ ቢሮን ጨምሮ ትኩረት መሳብ ችሏል።

በአመቱ 12 ማይል ርቀት መላክ የሚችል የገመድ አልባ ቴሌግራፍ መስራት ቻለ። የፈጠራ ባለቤት መብትን ለማግኘትም አመለከተ። ቀጥሎም ንግስት ቪክቶሪያ ከልጃቸው ከልኡል ኤድዋርድ መልእክት መላክ የሚችሉበትን ፈጠራ ሰራ።

በብዙ ፊዚስቶች ይታመን የነበረውን የሬድዮ ሞገዶች የሚጓዙት ቀጥታ መስመር ነው የሚል እሳቤ የሚሞግት እቅድ ነደፈ። የፈጠራ ስራውን በማሻሻል የአትላንቲክ ውቅያኖስን እንዲያቋርጥ የማድረግ ውጥን። በአትላንቲክ ውቅያኖስ ላይም የተሳካ ሙከራውን አድርጓል።

በአትላንቲክ ውቅያኖስ ላይ ያደረገው ሙከራም የሬድዮ ሞገዶችን በአለም ዙሪያ መላክ እንደሚቻል ፍንጭ የሰጠ ሙከራው ነው። ማርኮኒ ለገመድ አልባ የቴሌግራፍ ፈጠራው በአውሮፓውያኑ 1909 የኖቤል ሽልማትን ከጀርመኑ ፊዚስት ካርል ኤፍ ብራውን ተጋርቷል።

ጉግሊሞ ማርኮኒ የሬድዮ ሞገድን በመጠቀም በፈጠረው የተግባቦት ግኝትም የሬድዮ አባት ተብሎም ይጠራል። የማርኮኒን ፈጠራ መርከበኞች ከተጓዦች ጋር መጠቀም ጀምረውም ነበር። በሂደትም ማርኮኒ የጀመረው ግኝት በመሻሻል አስፈላጊ እና በየጊዜው ጥቅሙ የሚጨምር ፈጠራ ሁኗል።

የማርኮኒ ፈጠራ ከግዙፍ የበረዶ ግግር ጋር ተጋጭታ ለመስመጥ የተዳረገችው ግዙፏ እና ቅንጡዋ ታይታኒክ መርከብ ላይም አገልግሎት ላይ እንዲውል ተደረጎ ነበር።

የማርኮኒ ፈጠራ መርከቦች የርሱን ሬድዮ በመጠቀም ከተጓዦች ጋር በመግባባት የመቶዎችን ተጓዦችን ህይወት ማዳን አስችሏል። ፈጠራው በመስመጥ ላይ ከነበረችው ታይታኒክም ላይ ቢሆን ተራፊዎችን ለማዳን ትልቅ እገዛ አድርጓል።

የገመድ አልባ የተግባቦት ቴክኖሎጂ ፈጠራ ጀማሪ ብሎም የሬድዮ አባት ተብሎ የሚጠራው ጉግሊሞ ማርኮኒ በፈረንጆቹ 1935 ሲያርፍ ለክብሩ ሲባል በአሜሪካ፣ በእንግሊዝ እና በጣሊያን የነበሩ የሬድዮ ጣቢያዎች ለብዙ ደቂቃዎች ዝም እንዲሉ ተደርጓል።

በአብርሃም በለጠ
2022-06-02