በዓለማችን ላይ ዘጠኝ ሀገራት የኒወክሌር ጦር መሳሪያ አላቸው።
ከእነሱም መካከል ሩሲያ ትጠቀሳለች።
ሩሲያ ባገኘችባቸው አጋጣሚዎች ሁሉ በሚሳኤል ላይ ስትከውናቸው ስለሰነበተችው ተደጋጋሚ ሙከራ ስትናገር ቆይታለች።
ሩሲያ “ሃይፐርሶኒክ ዚርኮን ክራይዝ” የተሰኘውን የሚሳኤሏን ሙከራ ማጠናቀቋን ገልጻለች።
በዚህም ሩሲያ በጦርነት ውስጥ ውጤት ቀያሪ እንደሆነ የሚነገርለትን ይህን አይነት ሚሳዔል በመሞከር ከቀዳሚዋ ሀገር ለመሆን ችላለች።
ዚርኮን ሩሲያ “የጠላት” ብላ በምትጠራቸው መርከቦች እና የምድር ላይ ኢላማዎች ጥቅም ላይ እንደሚውል ይታወቃል።
ከጎርጎሮሳውያኑ አመት መጨረሻ በፊት ሚሳኤሏን በሰሜናዊ የጦር መርከቦች ላይ ታሰማራለች ተብሎ እንደሚጠበቅ አንድ ከፍተኛ ወታደራዊ ባለስልጣን ረቡዕ ተናግረዋል።
የሩሲያ ሰሜን አዛዥ አሌክሳንደር ሞይሴዬቭ ፣አድሚራል ጎሎቭኮ መርከብ ዚርኮንን ሲታጠቅ የመጀመሪያው ይሆናል መባሉን TASS የዜና ወኪል ዘግቧል።
አድሚራል ጎርሽኮቭ የተሰኘው የሩስያ ፕሮጀክት በሴንት ፒተርስበርግ በሴቨርናያ ቨርፍ ለሩሲያ የባህር ኃይል በ250 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር የተገነባ እንደሆነ ይታወቃል።
ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ዚርኮን ከድምፅ ፍጥነት በዘጠኝ እጥፍ ይበልጣል ፤ ተወዳዳሪ የሌለው የጦር መሳሪያ አካል ነው ሲሉ አሞካሽተውታል።
ሩሲያ በዩክሬን ለሶስት ወራት ባካሔደችው ጦርነት ከፍተኛ ኪሳራ ደርሶባታል ብትባልም ሀገሪቱ ግን አዳዲስ ሚሳኤሎቿን በመሞከር ደፋ ቀና እያለች ነው ሲል ሮይተርስ ጽፏል።
በባሬንትስ ባህር ላይ ከነበረች መርከብ በነጭ ባህር 1 ሺሕ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ለመድረስ የተተኮሰችው የዚርኮን ሚሳኤል በተሳካ ሁኔታ ኢላማዋን እንደመታች የመከላከያ ሚኒስቴር ባሳለፍነው ሳምንት ጠቁሟል።
ሚሳኤሉ እስከ 1 ሺሕ ኪሎ ሜትር ርቆ ያለን ኢላማ መመታት የሚችል ሲሆን በሰዓት ከ6,000 ኪሎ ሜትር በላይ ይምዘገዘጋል።
ሩሲያ 5 ሺሕ 976 የኒውክሌር ክምችት እንዳለት መረጃዎች ይጠቁማሉ። ነገር ግን ሁሉም ለግዳጅ ብቁ የሆኑና በረዥም ርቀት የሚምዘገዘጉ አይደሉም።
እስከ 16 ሺሕ ኪሎ ሜትር ርቀት መመዘግዘግ የሚችል አህጉር አቋርጭ ሚሳኤል እንዳለትም ይነገራል።
ሚሳኤሎች ከፍተኛ ውድመት እንዲያደርሱ ተደርገው በመሰራታቸው ሲተኮሱ ከፍተኛ ኃይል ያለው ብርሃን ስለሚወጣ ፈንዳታው የሚፈጥረው የኃይል ንዝረት ሕንጻዎችን ጨምሮ በዙሪያው የሚያገኘውን ሁሉ ዶጋ አመድ ያደርጋል።
ሩሲያ ምዕራባያኑን በሴኮንዶች ማጥፋት የሚችል የኒውኩሌር ሚሳኤል ልምምድ ለማድረግ ሽር ብትን እያለች እንደሆነ ማስታወቋ አይዘነጋም ።
በመቅደስ እንዳለ
2022-06-02
