ሀገሬ ቲቪ

ኮቪድ 19ኝን መረመርኩ ብሎ ያጭበረበረው ወጣት

ከህንድ ፖሊሶች ዱላ፤ ለተከተበ በሬ ሸልማለው እስካለችው እስያዊት ሀገር ድረስ ኮቪድ ቫይረስ በርካታ ግርምትን ያጫሩብንን ተግባራት አስመልክቶናል።

ከዚህ ቀደም 60 ግዜ የኮቪድ ቫይረስ መከላከያ ክትባቶችን ስለወሰደው ሰው ነግረናችሁ ነበር። ይህኛው ወይ ጉድ ብቻም ሳይሆን እንዴት ያለ ድፍረት ነውም ያሰኛል።

አንድ በለጋ እድሜላይ የሚገኝ ልጅ ሀሰተኛ የኮቪድ መመርመሪያ ማዕከል ከልቶ በርካቶችን አጭበርብሯል መባሉን ሰማን። ይህ ጀርመናዊ ታዳጊ ገና 17 ዓመቱ ነው። በከፈተው የኮቪድ መመርመሪያ ማዕከል ወደ 6 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብን የግሉ አድርጓል።

በጀርመን የኮቪድ 19 ቫይረስ ከታየበት ግዜ አንስቶ የቫይረሱ በከፍተኛ ፍጥነት መዛመት የሀገሪቱ መንግስት ከሚያደርገው የልየታ ምርመራ ውጪ በግል ተቋማት አገልግሎቱ እንዲሰጥ አስገድዷል።

ጀርመን የዜጎቿን የህክምና ወጪ በጤና መድን የምትሸፍን ሀገር ነች። ይህ አጋጣሚ ለበርካታ የጤና ተቋማት መልካም እድልን ፈጥሯል። ኮቪድ 19 በእጅጉ በተዛመተበት እንደ ምዕራባውያኑ በ2020 የ17 ዓመቱ ታዳጊ አንድ ሀሰብ በአዕምሮው ብቅ ይልበታል። ነገሩ ገንዘብ ለማግኘት በጣም ቀላሉ አማራጭ እንደሆነም ያምናል።

ምክንያቱ ደግሞ የኮቪድ ማዕከል ለመክፈት የሚያስፈልገው፤ እዚህ የኮቪድ ምርመራ አለ የሚል ታፔላ በካርቶኒ ላይ ፅፎ በደጃፉ ላይ መለጠፍ እና ለሚያደርጋቸው የኮቪድ ምርመራዎች ደረሰኞችን መቁረጥ ብቻ ነበር።

በዚህም ከመንግስት ረብጣ ብሮችን ማግኘት ይችላል። ወጣቱ አላቅማማም ኮቪድን እመረምራለው ሲል ማስታወቂያ ለጠፈ ከዛም 5.7 ሚሊዮን ዩሮ ወይም 6 ሚሊዮን ዶላር ወደ ቋት ማስገባት ቻለ።

የወጣቱ ድፍረት ይላል የጀርመን የህዝብ አቃቤ ህግ ፅህፈት ቤት፤ የወጣቱ ድፍረት በሌለው ሙያ፣ በሌለ ላቡራቶሪ ሰዎችን እመረምራለው ማለቱ ነው።

የወጣቱ ድፍረት ይህ ብቻም አይደለም ይላል ተቋሙ፤ በ2021 ሁለት ወራት ውስጥ ብቻ በቀን እስከ 5 ሺሕ ሰዎችን መርምሬያለው ሲል ሪፖርትም አድርጓል።

እንደምዕራባውያኑ የዘመን ስሌት ከ 2020 እስከ 2021 በነበረው ግዜ የሀገሬው መንስት የዜጎቹን የመመርመር መጠን ለማሳደግ በማሰብ የቁጥጥር ስራውን ከራሱ እጅ አውጥቶ ለዶክተሮች ማህበር አሳልፎ ሰጥቷል።

ይህ ውሳኔ እንዲህ ላሉ ወጣቶች የማጭበርበሪያ እድልን ከፍቶላቸዋል ብሏል። ከ4 ወራት ባነሰ ግዜ ውስጥ ወጣቱ 500 ሺሕ ሰዎችን መርምሬያለው ብሎ ሪፖርት አቀረበ በኢንተርኔት አማካኝነት። ከመንግስት ካዝናም ለወጣቱ 6 ሚሊዮን ዶላር ለተደረገው ምርመራ ተላልፏል።

ነገሩ ያላማረው አንድ የባንክ ሰራተኛ ከአንድ ታዳጊ ተማሪ አካውንት ውስጥ ይህንን ያህል መጠን ያለው ገንዘብ እንዴት ሊገኝ ይችላል ሲል ለፖሊስ ያመለክታል።

ፖሊሶችም ባደረጉት ማጣራት አጭበርባሪውን ወጣት በቅቁጥጥር ስር አውለውታል። አሁን የ19 አመቱ ወጣት በወንጀል ተፈርዶበታል። እንደ እድል ሆኖ፣ ማጭበርበሩን ሲፈፅም ገና 18 ዓመት ሳይሞላው ነበር እና ለአካለ መጠን ሳይደርስ የፈፀመው በመሆኑ በገንዘብ ቋቱ የሰበሰበውን ገንዘብ እንዲመልስ እና 1,600 ዶላር ቅጣት እንዲከፍል ተወስኖበታል። .

በሳምሶን ገድሉ
2022-06-02