ኢትዮጵያ ዕምቅ የተፈጥሮ ሀብቶች ባለቤት መሆኗ ሲነገር ቆይቷል፡፡ ይሁን እንጂ አሁንም ድረስ ያላትን የተፈጥሮ ሀብት በማስተዋወቅ ና አስመዝግባም ባለቤት ከመሆን አኳያ በበቂ ሁኔታ ስትንቀሳቀስ አትታይም።
ኖርዲክ ትሬዲንግ ኃላ/የተ/የግ/ማኅበር “የኢትዮጵያ ስጦታዎች” የተሰኘ ዓለም ዓቀፍ ፌስቲቫል ለማካሄድ ዝግጅት ማጠናቀቁን በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቋል።
ማኅበሩ በሃገር ውስጥ እና በውጪ ሃገራት የተለያዩ ማህበራዊ ኪነጥበባዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያላቸውን ዝግጅቶች በማከናወን ልምድና ሙያ ባላቸው የዘርፉ ባለሙያዎች የተደራጀ ተቋም ነው።በተቀረው ዓለም ያለውን የተዛባና የተሳሳተ አመለካከት ሊቀርፍ የሚያስችል ብሎም የሀገር ገፅታን የሚያግዝ ፌስቲቫል ለማካሔድ መሰናዳቱ ነው የተገለጸው።
ዝግጅቱ የሀገሪቱን ጤፍን፣ እንጀራንና ባህላዊ ምግቦችን ፤የባህላዊ ትውፊትን፣ የቡና ስርዓትን እና ሌሎች የሃገሪቱን መለያና መገለጫዎችን ለማስመዝገብ ና ለማስተዋወቅ እንደምንቀቃስ እወቁልኝ ብሏል።ይሄንን ፕሮግራም ከማኅበሩ ጋር በተባባሪነት ከሚያጋጁት መካከል ጋዜጠኛ አበበ ፈለቀ (ኢትዮ ፕሮሞሽን) ከአሜሪካ፣ አፍሮናውት ኢንተርቴይመንት ፤ ከጀርመን ሜስ ኤቨንትስ እንደሚገኙበት ተሰምቷል።የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ በተለያዩ ምርቶች ላይ ለተሰማሩ አምራችና ላኪዎች የገበያ እድል እንዲያገኙና የቱሪዝምና ኢንቨስትመንት ፍሰትን ወደ ሀገሪቱ ለመጨመር ይረዳል ብለዋል።
የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ስለሺ ግርማ በበኩላቸው ከዚህ ቀደም የቱሪዝም ዘርፉ ራሱን ችሎ ባለመደራጀቱ በሚጠበቀው ልክ ሳይንቀሳቀስ መቆየቱን ጠቅሰው ፌስቲቫሉን ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እንደሚደግፍ ተናግረዋል።
ኖርዲክ ትሬዲንግ ኃላ/የተ/የግ/ማኅበር ስራ አስፈጻሚ አቶ አንድነት በቀለ የኢትዮጵያን ጤፍ በዓለም አቀፍ ገበያ ላይ እንዳይቀርብ እንቅፋት ሆኖባት የቆየውን የባለቤትነት ጉዳይ በተመለከት ወደ ኔዘርላንድ አቅንተን የምንከውነው ጉዳይ አለን ብለዋል።
ከአንድ ወር በኋላ በጀርመን፣ አሜሪካ፣ ካናዳና በተለያዩ የዓለም ሀገሮች እንደሚካሄድ ታውቋል።
በፌስቲቫሉ ማስጀመሪያ መርኃ ግብር ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ ዓለም ዐቀፍ የማኅበረሰብ ክፍሎችና ታዋቂ ግለሰቦች በተገኙበት በወዳጅነት አደባባይ ተካሂዷል።
በዝግጅቱ ማስጀመሪያ የጥበብ፣ ግብርና፣ ዕደ ጥበብ፣ የቡና አፈላልና ሌሎች ትዕይንቶች ለእይታ ቀርበዋል።
በመቅደስ እንዳለ
2022-06-03
