የብሔራዊ ደም ባንክ አገልግሎት ፕላትሌት የተሰኘው ደም አይነት እጥረት አጋጥሟል አለ፡፡
ደም ባንኩ ከዚህ ቀደም በጾም ወራት ለ5 ቀናት ብቻ የሚበቃ ክምችት እንዳለው ለሀገሬ ቴሌቭዥን በተናገረው መሰረት መዘገቡ አይዘነጋም፡፡
መጠነኛ መሻሻል በማሳየት ቀደም ሲል በአማካኝ 200 ከረጢት ይሰበሰብ የነበረው አሁን ላይ ከ350 እስከ 400 ከረጢት ደርሷል ብለውናል የብሔራዊ ደም ባንክ አገልግሎት የኮሚውኒኬሽን ዳይሬክተር ዶ/ር ተመስገን አበጀ ይሁን እንጂ ፕላትሌት የተሰኘው ደም አይነት እጥረት ማጋጠሙን ነግረውናል፡፡የደም አይነቱ በባህሪው ከአምስት ቀን በላይ የማይቆይ በመሆኑ ለብልሽት ይዳረጋል ይላሉ፡፡
መጪው ጊዜ ክረምት እንደመሆኑ የትምህርት ቤቶች እና የተቋማት መዘጋት የደም ለጋሾችን ቁጥር ይቀንሳል ያሉት ኃላፊው ሕብረተሰቡ በማዕከልም ሆነ በተንቀሳቃሽ ክሊኒኮች በመሄድ ደም እንዲለግሱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በፍሬህይወት ታደሰ
2022-06-03
